1. ባስልኤል ርዝመቱ ሁለት ክንድ ተኩል፣ ወርዱ አንድ ክንድ ተኩል፣ ከፍታው አንድ ክንድ ተኩል የሆነ ታቦት ከግራር ዕንጨት ሠራ።
2. በውስጥና በውጭ በንጹሕ ወርቅ ለበጠው፤ በዙሪያውም የወርቅ ክፈፍ አበጀለት።
3. አራት የወርቅ ቀለበቶችን ሠርቶ ሁለት ቀለበቶችን በአንድ በኩል፣ ሁለት ቀለበቶችንም በሌላ በኩል አድርጎ ከአራቱ እግሮቹ ጋር አያያዛቸው።
4. ከዚያም መሎጊያዎችን ከግራር ዕንጨት ሠርቶ በወርቅ ለበጣቸው።
5. መሎጊያዎቹንም መሸከሚያ እንዲሆኑ በታቦቱ ጐንና ጐን ባሉት ቀለበቶች ውስጥ አስገባቸው።