ዘፀአት 35:5-22 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

5. ካላችሁ ንብረት ሁሉ ለእግዚአብሔር (ያህዌ) መሥዋዕት አቅርቡ፤ ፈቃደኛ የሆነ ማንም ለእግዚአብሔር (ያህዌ) የወርቅ፣ የብር፣ የናስ መባ ያምጣ፣

6. ሰማያዊ፣ ሐምራዊና ቀይ ማግ፤ ቀጭን ሐር፣ የፍየል ጠጒር፣

7. ቀይ የተነከረ የአውራ በግ ቆዳ፣ እንዲሁም አቆስጣ ቆዳ፣ የግራር ዕንጨት፤

8. ለመብራት የወይራ ዘይት፣ ለቅብዐ ዘይቱና ለጣፋጭ ሽታ ዕጣን ቅመም፤

9. በኤፉዱና በደረት ኪሱ ላይ የሚሆኑ መረግዶችና ሌሎች ዕንቍዎችን መባ አድርጎ ያምጣ።

10. “በመካከላችሁ ጥበበኞች የሆኑ ሁሉ መጥተው እግዚአብሔር (ያህዌ) ያዘዘውን ሁሉ ይሥሩ፤

11. የመገናኛውን ድንኳን ከነድንኳኑና ከነመደረቢያው፣ ማያያዣዎችን፣ ክፈፎችን፣ አግዳሚዎችን፣ ቋሚዎችንና መሠረቶችን፤

12. ታቦቱን ከነመሎጊያዎቹ፣ የስርየት መክደኛውንና የሚሸፍነውን መጋረጃ፤

13. ጠረጴዛውን ከነመሎጊያዎቹ፣ ዕቃዎቹን ሁሉና የሀልዎቱን ኅብስት፤

14. ለመብራት የሆነውን መቅረዝ ከነዕቃዎቹ፣ ቀንዲሎችንና ለመብራት የሚሆነውን ዘይት፤

15. የዕጣን መሠዊያውን ከነመሎጊያዎቹ፣ ቅብዐ ዘይቱንና ጣፋጭ ሽታ ያለውን ዕጣን፤ በመገናኛው ድንኳን ደጃፍ ላይ የሚሆነውን የመግቢያ መጋረጃ፤

16. የሚቃጠል መሥዋዕት መሠዊያውን ከናስ መጫሪያው፣ መሎጊያዎቹንና ዕቃዎቹን ሁሉ፣ የናስ ሰኑን ከነማስቀመጫው፣

17. ያደባባዩን መጋረጃዎች ከነምሶሶዎቻቸውና ከነመሠረቶቹ፣ ያደባባዩን መግቢያ መጋረጃ፤

18. ለመገናኛው ድንኳንና ለአደባባዩ የሚሆኑ የድንኳን ካስማዎችና ገመዶቻቸው፤

19. በመቅደሱ ውስጥ ለማገልገል የሚለበሱ የፈትል ልብሶችን ይኸውም የካህኑ የአሮንን የተቀደሱ ልብሶችንና ካህናት ሆነው ሲያገለግሉ የሚለብሷቸውን የወንዶች ልጆቹን ልብሶች ይሥሩ።”

20. ከዚያም የእስራኤል ማኅበረሰብ ሁሉ ከሙሴ ፊት ወጡ፤

21. ፈቃደኛ የነበረና ልቡን ያነሣሣው ሁሉ በመምጣት ለመገናኛው ድንኳን ሥራ፣ ለአገልግሎቱ ሁሉና ለተቀደሱ ልብሶች የሚሆን ለእግዚአብሔር (ያህዌ) መባ አመጡ።

22. ፈቃደኛ የነበሩ ሁሉ፣ ወንዶችም ሴቶችም መጥተው ከሁሉም ዐይነት የወርቅ ጌጦች አመጡ የአፍንጫ ጌጦችን፣ ሎቲዎችን፣ ቀለበቶችን፣ ድሪዎችንና ጌጣጌጦችን ሁሉ አመጡ፤ ሁሉም ወርቃቸውን እንደሚወዘወዝ መሥዋዕት ለእግዚአብሔር (ያህዌ) አቀረቡ።

ዘፀአት 35