ዘፀአት 35:1-7 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

1. ሙሴ የእስራኤልን ማኅበረሰብ ሁሉ ሰብስቦ እንዲህ አላቸው፤ “እግዚአብሔር (ያህዌ) እንድትፈጽሟቸው ያዘዛችሁ ነገሮች እነዚህ ናቸው፤

2. ስድስት ቀን ሥራ ይሠራል፤ ሰባተኛው ቀን ግን ለእግዚአብሔር (ያህዌ) የሰንበት ዕረፍት፣ የተቀደሰ ቀን ይሆንላችኋል፤ በዕለቱ ማናቸውንም ዐይነት ሥራ የሚሠራ ቢኖር ሞት ይገባዋል።

3. በሰንበት ቀን በማናቸውም መኖሪያዎቻችሁ ውስጥ እሳት አታንድዱ።”

4. ሙሴ ለእስራኤላውያን ማኅበረሰብ ሁሉ እንዲህ አላቸው፤ “እግዚአብሔር (ያህዌ) ያዘዘው ይህ ነው፤

5. ካላችሁ ንብረት ሁሉ ለእግዚአብሔር (ያህዌ) መሥዋዕት አቅርቡ፤ ፈቃደኛ የሆነ ማንም ለእግዚአብሔር (ያህዌ) የወርቅ፣ የብር፣ የናስ መባ ያምጣ፣

6. ሰማያዊ፣ ሐምራዊና ቀይ ማግ፤ ቀጭን ሐር፣ የፍየል ጠጒር፣

7. ቀይ የተነከረ የአውራ በግ ቆዳ፣ እንዲሁም አቆስጣ ቆዳ፣ የግራር ዕንጨት፤

ዘፀአት 35