13. በእኔ ደስ ተሰኝተህ ከሆነ፣ አንተን ዐውቅህና ያለ ማቋረጥ በፊትህ ሞገስ አገኝ ዘንድ መንገድህን አስተምረኝ፤ ይህ ሕዝብ የአንተ ሕዝብ መሆኑን አስታውስ።”
14. እግዚአብሔር (ያህዌ) “ሀልዎቴ ከአንተ ጋር ይሄዳል፤ ዕረፍትም እሰጥሃለሁ” ብሎ መለሰ።
15. ከዚያም ሙሴ እንዲህ አለው፤ “ሀልዎትህ ከእኛ ጋር ካልሄደ ከዚህ አትስደደን።
16. አንተ ከእኛ ጋር ካልሄድህ፣ አንተ በእኔና በሕዝብህ መደሰትህን ሌላው እንዴት ያውቃል? እኔንና ሕዝብህንስ በገጸ ምድር ከሚገኙት ከሌሎቹ ሕዝቦች ሁሉ ልዩ የሚያደርገን ሌላ ምን አለ?”
17. እግዚአብሔርም (ያህዌ) ሙሴን፣ “በአንተ ደስ ስላለኝና በስም ስለማውቅህ፣ የጠየቅኸውን ያንኑ አደርጋለሁ” አለው።
18. ከዚያም ሙሴ “እባክህ፤ ክብርህን አሳየኝ” አለው።
19. እግዚአብሔር (ያህዌ) እንዲህ አለ፤ “መልካምነቴ ሁሉ በፊትህ እንዲያልፍ አደርጋለሁ፤ በፊትህም ስሜን እግዚአብሔርን (ያህዌ) ዐውጃለሁ፤ ለምምረው ምሕረት አደርጋለሁ፤ ለምራራለትም ርኅራኄ አደርጋለሁ፤
20. ነገር ግን፣ ማንም እኔን አይቶ መኖር ስለማይችል፣ ፊቴን ማየት አትችልም።
21. ከዚያም እግዚአብሔር (ያህዌ) እንዲህ አለ፤ “በአጠገቤ ስፍራ አለ አንተም በዐለት ላይ ትቆማለህ፤
22. ክብሬ በዚያ ሲያልፍ በዐለቱ ስንጥቅ ውስጥ አደርግሃለሁ፤ በዚያም እስከ ማልፍ ድረስ በእጄ እጋርድሃለሁ፤