ዘፀአት 31:2-12 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

2. “እነሆ፤ ከይሁዳ ነገድ የሆር የልጅ ልጅ የሆነውን የኡሪን ልጅ ባስልኤልን መርጬዋለሁ።

3. በሁሉም ዐይነት የእጅ ጥበብ ሥራ፣ ብልሃት፣ ችሎታና ዕውቀት እንዲኖረው የእግዚአብሔርን (ኤሎሂም) መንፈስ ሞልቼዋለሁ፤

4. ይኸውም በወርቅ፣ በብርና በናስ ለሚሠሩት ሥራዎች በጥበብ የተሠሩ ጌጦችን እንዲያበጅ፣

5. ድንጋዮችን እንዲቆፍርና እንዲጠርብ ከዕንጨትም ጥርብ እንዲያወጣ፣ ሁሉንም ዐይነት የእጅ ጥበብ ሥራዎችን እንዲያከናውን ነው።

6. በተጨማሪም ከዳን ነገድ የሆነውን የአሂሳሚክን ልጅ ኤልያብን እንዲረዳው መርጬዋለሁ፤ እንዲሁም ያዘዝሁህን ሁሉ ያደርጉ ዘንድ ለእጅ ጥበብ ዐዋቂዎች ሁሉ ብልሃትን ሰጥቻቸዋለሁ፤

7. ይኸውም የመገናኛውን ድንኳን፣ የምስክሩን ታቦት በላዩ ላይ ካለው ከስርየት መክደኛው ጋር፣ ሌሎች የድንኳኑን መገልገያ ዕቃዎች ሁሉ፣

8. ጠረጴዛውን ከነዕቃዎቹ፣ ከንጹሕ ወርቅ የተሠራውን የወርቅ መቅረዝ ከነዕቃዎቹ፣ የዕጣኑን መሠዊያ፣

9. የሚቃጠል መሥዋዕት መሠዊያውን ከነዕቃዎቹ፣ ሰኑን፣ ከነማስቀመጫው፣

10. ከፈትል የተሠሩ ልብሶችን ይኸውም የካህኑን የአሮንን የተቀደሱ ልብሶችንና ካህናት ሆነው ሲያገለግሉ የሚለብሷቸውን የወንድ ልጆቹ ልብሶች፣

11. እንዲሁም የመቅደሱ የሆነውን ቅብዐ ዘይትና ጣፋጭ ሽታ ያለውን ዕጣን እንዲሠሩ ነው፤ ልክ እኔ እንዳዘዝሁህ ያብጇቸው።

12. ከዚያም እግዚአብሔር (ያህዌ) ሙሴን እንዲህ አለው፤

ዘፀአት 31