1. ዕጣን የሚጤስበት መሠዊያ ከግራር ዕንጨት ሥራ።
2. ርዝመቱና ጐኑ ባለ አንድ አንድ ክንድ የሆነ ከፍታውም ሁለት ክንድ የሆነ አራት ማእዘን ይሁን፤ ከመሠዊያው ጋር አንድ ወጥ የሆኑ ቀንዶች ይኑሩት።
3. ላዩን፣ ጐኖቹን ሁሉና ቀንዶቹን በንጹሕ ወርቅ ለብጣቸው፤ ዙሪያውን የወርቅ ክፈፍ አብጅለት።
4. መሠዊያውን ለመሸከም የሚያገለግሉትን መሎጊያዎች የሚይዙ፣ ከክፈፉ በታች ትይዩ የሆኑ ሁለት የወርቅ ቀለበቶችን ለመሠዊያው አብጅ።
5. መሎጊያዎቹንም ከግራር እንጨት ሠርተህ በወርቅ ለብጣቸው።
6. መሠዊያውን ከመጋረጃው ፊት ለፊት፣ ይኸውም ከምስክሩ ታቦት ፊት፣ ከምስክሩ በላይ ካለው እኔ አንተን ከምገናኝበት ከስርየት መክደኛው ፊት አስቀምጠው።
7. “አሮን መብራቶቹን በሚያዘጋጅበት ጊዜ፣ በየማለዳው ደስ የሚያሰኝ ሽታ ዕጣን በመሠዊያው ላይ ያጢስ።
8. ምሽት ላይ መብራቶቹን በሚያበራበትም ጊዜ ዕጣኑን ማጠን አለበት፤ ይኸውም በሚመጡት ትውልዶች ሁሉ ዕጣኑ በእግዚአብሔር (ያህዌ) ፊት ዘወትር እንዲጤስ ነው።
9. በዚህም መሠዊያ ላይ ሌላ ዕጣን ወይም ሌላ የሚቃጠል መሥዋዕት ወይም የእህል መሥዋዕት አታቅርብ፤ የመጠጥ መሥዋዕትም አታፍስበት።