2. እዚያም የእግዚአብሔር (ያህዌ) መልአክ በቍጥቋጦው ውስጥ በሚንቀለቀል የእሳት ነበልባል መካከል ተገለጠለት። ሙሴም ቍጥቋጦው በእሳት ቢያያዝም እንኳ፣ አለ መቃጠሉን አየ።
3. ሙሴም፣ “ቍጥቋጦው ለምን እንደማይቃጠል ቀረብ ብዬ ይህን አስገራሚ ነገር ልመልከት” አለ።
4. ሙሴ ሁኔታውን ለመመልከት መቅረቡን እግዚአብሔር (ያህዌ) ባየ ጊዜ፣ ከቍጥቋጦው ውስጥ እግዚአብሔር (ኤሎሂም) “ሙሴ፣ ሙሴ” ብሎ ጠራው፤ ሙሴም “አቤት እነሆኝ” አለው።
5. እግዚአብሔርም (ኤሎሂም)፣ “ወደዚህ እንዳትቀርብ፤ ይህች የቆምኽባት ምድር የተቀደሰች ስለሆነች ጫማህን አውልቅ” አለው
6. ቀጥሎም፣ “እኔ የአባቶችህ የአብርሃም፣ የይስሐቅ፣ የያዕቆብ አምላክ (ኤሎሂም) ነኝ” አለው። በዚህ ጊዜ ሙሴ እግዚአብሔርን (ኤሎሂም) ፊት ለፊት ማየት ስለ ፈራ ፊቱን ሸፈነ።
7. ከዚያም እግዚአብሔር (ያህዌ)፣ እንዲህ አለ “በግብፅ አገር የሚኖሩትን የሕዝቤን መከራ አይቻለሁ፤ ከአሠሪዎቻቸው ጭካኔ የተነሣ የሚያሰሙትንም ጩኸት ሰምቻለሁ፤ ሥቃያቸውንም ተረድቼአለሁ።
8. ስለዚህም ከግብፃውያን እጅ ልታደጋቸውና ማርና ወተት ወደምታፈሰው ሰፊና ለም ወደሆነችው ወደ ከነዓናውያን፣ ኬጢያውያን፣ አሞራውያን፣ ፌርዛውያን፣ ኤዊያውያንና ኢያቡሳውያን ምድር ላወጣቸው ወርጃለሁ።
9. አሁንም የእስራኤል ልጆች ጩኸት ወደ እኔ ደርሷል፤ ግብፃውያን የሚያደርሱባቸውን ግፍ አይቻለሁ።
10. በል እንግዲህ ና፤ ሕዝቤን፣ የእስራኤልን ልጆች ከግብፅ ምድር እንድታወጣቸው ወደ ፈርዖን እልክሃለሁ”።
11. ሙሴ እግዚአብሔርን (ኤሎሂም)፣ “ወደ ፈርዖን የምሄድና የእስራኤልን ልጆች ከግብፅ የማወጣ እኔ ማን ነኝ? አለው።
12. እግዚአብሔርም (ኤሎሂም)፣ “እኔ ከአንተ ጋር እሆናለሁ፤ እኔ የላክሁህ ለመሆኑ ምልክቱ ይህ ነው፤ ሕዝቡን ከግብፅ ካወጣሃቸው በኋላ በዚህ ተራራ ላይ እግዚአብሔርን (ኤሎሂም) ታመልካላችሁ” አለው።
13. ሙሴም እግዚአብሔርን (ኤሎሂም)፣ “ወደ እስራኤል ልጆች ሄጄ፣ ‘የአባቶቻችሁ አምላክ ወደ እናንተ ልኮኛል’ ስላቸው ‘ስሙ ማን ነው?’ ብለው ቢጠይቁኝ ምን እላቸዋለሁ?” አለው።
14. እግዚአብሔርም (ኤሎሂም) ሙሴን፣ “እኔ፣ ያለሁና የምኖር ነኝ (ያህዌ)፤ ስለዚህም፣ ‘ያለና የሚኖር’ ልኮኛል ብለህ ንገራቸው” አለው።
15. ደግሞም እግዚአብሔር (ኤሎሂም) ሙሴን፣ “የአባቶቻችሁ የአብርሃም አምላክ፣ የይስሐቅ አምላክ፣ የያዕቆብ አምላክ የሆነው እግዚአብሔር (ያህዌ) ወደ እናንተ ልኮኛል፤ ስሜም ለዘለዓለም ይኸው ነው፤ ወደ ፊት በተከታታይ በሚነሣው ትውልድ ሁሉ የምታሰበው በዚህ ስም ነው ብለህ ለእስራኤል ልጆች ንገራቸው” አለው።
16. “ሂድና የእስራኤልን አለቆች ሰብስበህ፣ የአባቶቻችሁ የአብርሃም፣ የይስሐቅና የያዕቆብ አምላክ የሆነው እግዚአብሔር (ያህዌ) ተገለጠልኝና እንዲህ አለኝ፤ ጐብኝቻችኋለሁ፤ በግብፅ የደረሰባችሁንም አይቻለሁ።
17. ስለዚህም በግብፅ ከምትቀበሉት መከራ አውጥቼ ማርና ወተት ወደምታፈሰው ወደ ከነዓናውያን፣ ወደ ኬጢያውያን፣ ወደ አሞራውያን፣ ወደ ፌርዛውያን፣ ወደ ኤዊያውያንና ኢያቡሳውያን ምድር አገባችኋለሁ ብሎአል ብለህ ንገራቸው” አለኝ።
18. “የእስራኤል አለቆችም ይሰሙሃል። አንተና የእስራኤል አለቆች ወደ ግብፅ ንጉሥ ትሄዱና፣ ‘የዕብራውያን አምላክ እግዚአብሔር (ያህዌ) ተገለጠልን፤ ስለዚህም ወደ ምድረ በዳ የሦስት ቀን መንገድ ተጒዘን ለአምላካችን ለእግዚአብሔር (ያህዌ) መሥዋዕት እንድናቀርብ ፍቀድልን’ ብላችሁ ትነግሩታላችሁ።