ዘፀአት 3:2-10 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

2. እዚያም የእግዚአብሔር (ያህዌ) መልአክ በቍጥቋጦው ውስጥ በሚንቀለቀል የእሳት ነበልባል መካከል ተገለጠለት። ሙሴም ቍጥቋጦው በእሳት ቢያያዝም እንኳ፣ አለ መቃጠሉን አየ።

3. ሙሴም፣ “ቍጥቋጦው ለምን እንደማይቃጠል ቀረብ ብዬ ይህን አስገራሚ ነገር ልመልከት” አለ።

4. ሙሴ ሁኔታውን ለመመልከት መቅረቡን እግዚአብሔር (ያህዌ) ባየ ጊዜ፣ ከቍጥቋጦው ውስጥ እግዚአብሔር (ኤሎሂም) “ሙሴ፣ ሙሴ” ብሎ ጠራው፤ ሙሴም “አቤት እነሆኝ” አለው።

5. እግዚአብሔርም (ኤሎሂም)፣ “ወደዚህ እንዳትቀርብ፤ ይህች የቆምኽባት ምድር የተቀደሰች ስለሆነች ጫማህን አውልቅ” አለው

6. ቀጥሎም፣ “እኔ የአባቶችህ የአብርሃም፣ የይስሐቅ፣ የያዕቆብ አምላክ (ኤሎሂም) ነኝ” አለው። በዚህ ጊዜ ሙሴ እግዚአብሔርን (ኤሎሂም) ፊት ለፊት ማየት ስለ ፈራ ፊቱን ሸፈነ።

7. ከዚያም እግዚአብሔር (ያህዌ)፣ እንዲህ አለ “በግብፅ አገር የሚኖሩትን የሕዝቤን መከራ አይቻለሁ፤ ከአሠሪዎቻቸው ጭካኔ የተነሣ የሚያሰሙትንም ጩኸት ሰምቻለሁ፤ ሥቃያቸውንም ተረድቼአለሁ።

8. ስለዚህም ከግብፃውያን እጅ ልታደጋቸውና ማርና ወተት ወደምታፈሰው ሰፊና ለም ወደሆነችው ወደ ከነዓናውያን፣ ኬጢያውያን፣ አሞራውያን፣ ፌርዛውያን፣ ኤዊያውያንና ኢያቡሳውያን ምድር ላወጣቸው ወርጃለሁ።

9. አሁንም የእስራኤል ልጆች ጩኸት ወደ እኔ ደርሷል፤ ግብፃውያን የሚያደርሱባቸውን ግፍ አይቻለሁ።

10. በል እንግዲህ ና፤ ሕዝቤን፣ የእስራኤልን ልጆች ከግብፅ ምድር እንድታወጣቸው ወደ ፈርዖን እልክሃለሁ”።

ዘፀአት 3