24. በእነዚህ ሁለት ማእዘኖች ላይ ከታች እስከ ላይ ድረስ ድርብ ሲሆኑ በአንድ ቀለበት ውስጥ የሚገጥሙ መሆን አለባቸው፤ በሁለቱም ወገን እንዲሁ መሆን አለበት።
25. ስለዚህ ስምንት ወጋግራዎች አሉ፤ እንዲሁም ዐሥራ ስድስት የብር መቆሚያዎች ሲኖሩ፣ ለእያንዳንዱ ወጋግራ ሁለት ሁለት መቆሚያ ይሆናል።
26. “ደግሞም ከግራር ዕንጨት አግዳሚዎችን አብጅ፤ በአንድ በኩል ላሉት የማደሪያው ድንኳን ወጋግራዎች አምስት፣
27. በሌላው ጎን ላሉት አምስት፣ በማደሪያው ድንኳን ዳር በምዕራብ በኩል ባሉት ወጋግራዎች አምስት አብጅ።
28. መካከለኛው አግዳሚ በወጋግራዎቹ መካከል ከጫፍ እስከ ጫፍ ይተላለፍ።
29. ወጋግራዎቹን በወርቅ ለብጣቸው፤ አግዳሚዎቹን ለመያዝ የወርቅ ቀለበቶች አብጅ፤ አግዳሚዎቹንም በወርቅ ለብጣቸው።
30. “ማደሪያ ድንኳኑንም በተራራው ላይ ባየኸው ዕቅድ መሠረት ትከለው።
31. “ከሰማያዊ፣ ከሐምራዊ፣ ከቀይ ማግና በቀጭኑ ከተፈተለ በፍታ መጋረጃ አብጅ፤ እጀ ብልህ ሠራተኛም ኪሩቤልን ይጥለፍበት።
32. በወርቅ በተለበጡ ከግራር ዕንጨት በተሠሩና በአራቱ የብር መቆሚያዎች ላይ በቆሙት በአራቱ ምሰሶዎች፣ በወርቅ ኵላቦች ላይ አንጠልጥለው።
33. መጋረጃውን በማያያዣዎቹ ላይ ስቀለው፤ የምስክሩንም ታቦት ከመጋረጃው በስተ ኋላ አስቀምጠው፤ መጋረጃውም መቅደሱን ከቅድስተ ቅዱሳኑ ይለያል።
34. በቅድስተ ቅዱሳኑ ውስጥ በምስክሩ ታቦት ላይ የማስተስረያውን ክዳን አስቀምጥ።