7. በኤፉድና በደረት ኪስ ላይ የሚሆኑ መረግዶችና ሌሎች ዕንቍዎች።
8. “ከዚያም መቅደስ እንዲሠሩልኝ አድርግ፤ እኔም በመካከላቸው አድራለሁ።
9. ማደሪያ ድንኳኑንና በውስጡ ያለውን ዕቃ ሁሉ ልክ እኔ በማሳይህ ዕቅድ መሠረት ሥሩት።
10. “ርዝመቱ ሁለት ክንድ ተኩል፣ ወርዱ አንድ ክንድ ተኩል፣ ከፍታው አንድ ክንድ ተኩል የሆነ ታቦት ከግራር እንጨት እንዲሠሩ አድርግ።
11. ውስጡንም ውጭውንም በንጹሕ ወርቅ ለብጠው፤ በዙሪያውም የወርቅ ክፈፍ አብጅለት።
12. አራት የወርቅ ቀለበቶች ሠርተህ ሁለቱን በአንድ በኩል ሁለቱን በሌላ በኩል ከአራቱ እግሮች ጋር አያይዝ።
13. ከዚያም መሎጊያዎችን ከግራር ዕንጨት ሥራ፤ በወርቅም ለብጣቸው።
14. መሎጊያዎችንም መሸከሚያ እንዲሆኑ በታቦቱ ማእዘኖች ላይ ባሉት ቀለበቶች ውስጥ አስገባቸው።
15. መሎጊያዎቹ ከታቦቱ ቀለበቶች ውስጥ ምንጊዜም መውጣት የለባቸውም።
16. የምሰጥህንም ምስክር በታቦቱ ውስጥ አኑር።
17. “ርዝመቱ ሁለት ክንድ ተኩል፣ ወርዱ አንድ ክንድ ተኩል የሆነ የስርየት መክደኛ ከንጹሕ ወርቅ ሥራለት።
18. በስርየት መክደኛው ዳርና ዳር ላይ የሚሆኑ ከወርቅ የተቀረጹ ሁለት ኪሩቤል ሥራ።
19. አንዱን ኪሩብ በአንደኛው፣ ሁለተኛውን ኪሩብ በሌላኛው ዳር አድርግ በሁለቱም ጫፎች ሁለቱን ኪሩቤል ከስርየት መክደኛው ጋር አንድ ወጥ አድርገህ ሥራቸው።