7. “አንድ ሰው ሴት ልጁን አገልጋይ እንድትሆን ቢሸጣት፣ እንደ ወንዶቹ አገልጋዮች በነጻ መሸኘት የለባትም።
8. ለእርሱ ትሆነው ዘንድ የመረጣትን ጌታዋን ደስ ባታሰኝ፣ በዎጆ ይስደዳት፤ ለባዕዳን ይሸጣት ዘንድ መብት የለውም፤ ምክንያቱም ለእርሷ ያለውን ታማኝነት አጓድሏልና።
9. ለወንድ ልጁ ትሆን ዘንድ መርጧት ከሆነ እንደ ራሱ ልጅ የሚገባትን መብት ይስጣት።
10. ሌላ ሴት ቢያገባ፣ ለመጀመሪያ ሚስቱ ምግቧን፣ ልብሷንና የጋብቻ መብቷን አይከልክላት።
11. እነዚህን ሦስት ነገሮች የማያሟላላት ቢሆን፣ ያላንዳች የገንዘብ ክፍያ በነጻ መሄድ ይኖርባታል።
12. “ሰውን ደብድቦ የገደለ ሞት ይገባዋል።
13. ሆኖም እግዚአብሔር (ኤሎሂም) ፈቅዶ ሰውየው ሳያውቅ በድንገት አድርጎት ከሆነ፣ እኔ ወደምወስነው ስፍራ ይሽሽ።
14. አንድ ሰው በተንኰል ሆን ብሎ ሌላውን ቢገድል፣ ከመሠዊያዬ ተወስዶ ይገደል።
15. “አባቱን ወይንም እናቱን የሚመታ ይገደል።
16. “አንዱ ሌላውን ጠልፎ የሸጠ ወይም በተያዘ ጊዜ ከእጁ ላይ የተገኘበት ይገደል።
17. “አባቱን ወይንም እናቱን የሚሰድብ ይገደል።
18. ሰዎች ተጣልተው አንዱ ሌላውን በድንጋይ ወይም በቡጢ ቢመታውና ተመቺው ሳይሞት በአልጋ ላይ ቢውል፣
19. በትሩንም ይዞ ደጅ ለደጅ የሚል ቢሆን፣ በዱላ የመታው ሰው አይጠየቅበትም፤ ሆኖም ለተጐጂው ሰው ለባከነበት ጊዜ ገንዘብ ይክፈል፤ ፈጽሞ እስኪድን ክትትል ያድርግለት።
20. “አንድ ሰው ወንድ ወይም ሴት ባሪያውን በዱላ ቢመታና ባሪያውም በዚህ የተነሣ ቢሞት መቀጣት አለበት፤
21. ነገር ግን ከአንድ ወይም ከሁለት ቀን በኋላ ባሪያው ቢነሣ መቀጣት የለበትም፤ ባሪያው ንብረቱ ነውና።