11. “እግዚአብሔር (ያህዌ) ከአማልክት ሁሉ በላይ ኀያል እንደሆነ አሁን ዐወቅሁ፤ እስራኤልን በትዕቢት ይዘው በነበሩት ሁሉ ላይ ይህን አድርጎአልና።”
12. ከዚያም የሙሴ አማት ዮቶር የሚቃጠል መሥዋዕትና ሌሎች መሥዋዕቶች ለእግዚአብሔር (ኤሎሂም) አቀረበ፤ አሮንም ከሙሴ አማት ጋር በእግዚአብሔር (ኤሎሂም) ፊት እንጀራ ለመብላት ከእስራኤል አለቆች ሁሉ ጋር መጣ።
13. በማግሥቱ ሙሴ ሕዝቡን ለመዳኘት ተቀመጠ፤ እነርሱም በዙሪያው ከጧት እስከ ማታ ድረስ ቆሙ።
14. አማቱም ሙሴ ለሕዝቡ የሚያደርገውን ሁሉ ባየ ጊዜ፣ “ምን ማድረግህ ነው? እነዚህ ሁሉ ሰዎች ከጧት እስከ ማታ በዙሪያህ ቆመው ሳለ፣ ብቻህን በፍርድ ወንበር ላይ ለምን ትቀመጣለህ?” አለው።
15. ሙሴም እንዲህ ብሎ መለሰለት፤ “ምክንያቱም ሰዎቹ የእግዚአብሔርን (ኤሎሂም) ፈቃድ በመፈለግ ወደ እኔ ይመጣሉ።
16. ክርክር በኖራቸው ቍጥር ጒዳያቸው ወደ እኔ ይመጣል፤ ለግራና ለቀኙ የሚሆነውን እኔ ወስኜ የእግዚአብሔርን (ኤሎሂም) ሥርዐትና ሕጎች እነግራቸዋለሁ።”
17. የሙሴ አማት መልሶ እንዲህ አለው። “የምትሠራው መልካም አይደለም።
18. አንተና ወደ አንተ የሚመጡት እነዚህ ሰዎች የምታደርጉት ነገር ቢኖር ራሳችሁን ማድከም ነው፤ ሥራው ለአንተ ከባድ ሸክም ነው፤ ብቻህን ልትወጣው አትችልም።
19. ምክር እሰጥሃለሁና አሁን እኔን አድምጠኝ፤ እግዚአብሔር (ኤሎሂም) ከአንተ ጋር ይሁን። አንተ በእግዚአብሔር (ኤሎሂም) ፊት (የሕዝብ ተወካይ መሆን አለብህ)፤ ክርክራቸውን ወደ እርሱ ታቀርባለህ።
20. ሥርዐቶቹንና ሕጎቹን አስተምራቸው፤ እንዴት መኖር እንዳለባቸውና ምን መሥራት እንደሚገባቸው አሳያቸው።
21. ነገር ግን ችሎታ ያላቸውን ሰዎች ከሕዝቡ ሁሉ ምረጥ፤ እነዚህም ሰዎች እግዚአብሔርን (ኤሎሂም) የሚፈሩ፣ ታማኞችና በማታለል የሚገኘውን ጥቅም የሚጸየፉ ይሁኑ። የሺህ፣ የመቶ፣ የአምሳ፣ የዐሥር፣ አለቃ አድርገህ ሹማቸው።