1. የምድያም ካህን የሙሴ አማት ዮቶር፣ እግዚአብሔር (ኤሎሂም) ለሙሴና ለሕዝቡ ለእስራኤል ያደረገላቸውን ሁሉ እንዲሁም እግዚአብሔር (ያህዌ) እስራኤልን ከግብፅ እንዴት እንዳወጣቸው ሰማ።
2. ሙሴ ሚስቱን ሲፓራን ከመለሳት በኋላ አማቱ ዮቶር እርሷንና ሁለት ወንድ ልጆቿን ተቀብሏቸው ነበር።
3. ሙሴ፣ “በባዕድ አገር መጻተኛ ነኝ” ለማለት የመጀመሪያ ልጁን ስም ጌርሳም አለው።
4. “የአባቴ አምላክ ረዳቴ ነው፤ ከፈርዖን ሰይፍ አድኖኛልና” ለማለት ደግሞ ሁለተኛውን ልጁን አልዓዛር አለው።
5. የሙሴ አማት ዮቶር ከሙሴ ወንድ ልጆችና ሚስት ጋር ሆኖ በምድረ በዳ ከእግዚአብሔር (ኤሎሂም) ተራራ አጠገብ ወደ ሰፈረበት ወደ ሙሴ መጣ።
6. ዮቶር፣ “እኔ አማትህ ዮቶር፣ ከሚስትህና ከሁለት ወንዶች ልጆቿ ጋር እየመጣን ነው” ሲል መልእክት ላከበት።
7. ስለዚህ ሙሴ አማቱን ሊቀበለው ወጣ፤ ዝቅ ብሎ እጅ በመንሣትም ሳመው፤ ከዚያም ሰላምታ ተለዋውጠው ወደ ድንኳኑ ገቡ።