ዘፀአት 16:21-31 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

21. በየማለዳው እያንዳንዱ የሚያስፈልገውን ያህል ሰበሰበ፤ ፀሓዩ እየበረታ በሄደም ጊዜ ቀለጠ።

22. ስድስተኛው ቀን ለእያንዳንዱ ሰው ሁለት ሁለት ጎሞር አድርገው እጥፍ ሰበሰቡ፤ የማኅበሩም አለቆች ወደ ሙሴ መጥተው ይህንኑ ነገሩት።

23. እርሱም አላቸው፤ “እግዚአብሔር (ያህዌ) ያዘዘው ይህ ነው፤ ‘ነገ እግዚአብሔር (ያህዌ)፣ የተቀደሰ ሰንበት በመሆን፣ የዕረፍት ቀን ይሆናል። ስለዚህ መጋገር የምትፈልጉትን ጋግሩ፤ መቀቀል የምትፈልጉትን ቀቅሉ። የተረፈውን አስቀምጡ፤ እስከ ጧትም ድረስ አቆዩት።

24. ስለዚህ ሙሴ እንዳዘዘው እስከ ጧት ድረስ አቆዩት፤ አልሸተተም፤ ወይም አልተላም።

25. ሙሴም እንዲህ አለ፤ “ዛሬውኑ ብሉት፤ ዛሬ የእግዚአብሔር (ያህዌ) ሰንበት ነውና። ዛሬ በመሬት ላይ ምንም አታገኙም።

26. ስድስት ቀን ትሰበስቡታላችሁ፤ በሰባተኛው ቀን በሰንበት ዕለት ግን ምንም ነገር አይኖርም።”

27. ሆኖም አንዳንዶቹ በሰባተኛው ቀን ለመሰብሰብ ወጡ፤ ነገር ግን ምንም አላገኙም።

28. ከዚያም እግዚአብሔር (ያህዌ) ሙሴን አለው፤ ትእዛዞቼንና መመሪያዎቼን ለመፈጸም እስከ መቼ እምቢ ትላላችሁ?

29. እግዚአብሔር (ያህዌ) ሰንበትን የሰጣችሁ መሆኑን ልብ በሉ፤ በስድስተኛው ቀን ለሁለት ቀን የሚሆን እንጀራ የሰጣችሁ ለዚህ ነው። በሰባተኛው ቀን እያንዳንዱ ሰው ባለበት ይቆይ፤ ማንም አይወጣም።”

30. ስለዚህ ሕዝቡም በሰባተኛው ቀን ዐረፉ።

31. የእስራኤልም ሕዝብ ምግቡን መና አሉት፤ እርሱም እንደ ድንብላል ዘር ነጭ፣ ጣሙም ከማር እንደ ተጋገረ ቂጣ ነበር።

ዘፀአት 16