ዘፀአት 15:6-16 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

6. “አቤቱ እግዚአብሔር (ያህዌ) ሆይ፤ቀኝ እጅህ በግርማ ከበረ፤አቤቱ እግዚአብሔር (ያህዌ) ሆይ፤ቀኝ እጅህ ጠላትን አደቀቀ።

7. በግርማህ ታላቅነት፣የተቃወሙህን ጣልኻቸው፤ቍጣህን ሰደድህ፤እንደ ገለባም በላቸው።

8. በአፍንጫህ እስትንፋስ፣ውሆች ተቈለሉ፤ፈሳሾችም እንደ ግድግዳ ቆሙ፤የጥልቁ ውሃ ባሕሩ ውስጥ ረጋ።

9. “ጠላት፣ ‘አሳድዳቸዋለሁ፤እማርካቸዋለሁ፤ምርኮን እካፈላለሁ፤ነፍሴ በእነርሱ ትጠግባለች፤ሰይፌን እመዛለሁ፤እጄም ትደመስሳቸዋለች አለ።

10. አንተ ግን እስትንፋስህን አነፈስህ፤ባሕርም ከደናቸው፤በኀያላን ውሆች፣እንደ ብረት ሰጠሙ።

11. “አቤቱ እግዚአብሔር (ያህዌ) ሆይ፤ከአማልክት መካከል፣ እንደ አንተ ማን አለ?በቅድስናው የከበረ፣በክብሩ የሚያስፈራ፣ድንቆችን የሚያደርግ፣እንደ አንተ ማን አለ?

12. ቀኝ እጅህን ዘረጋህ፤ምድርም ዋጠቻቸው።

13. ‘በማይለወጠው ፍቅርህ፣የተቤዥሃቸው ሕዝብህን ትመራለህ፤እነርሱን በብርታትህ፣ወደ ቅዱስ ማደሪያህ ትመራቸዋለህ።

14. አሕዛብ ይሰማሉ፤ ይንቀጠቀጡማል፤የፍልስጥኤምን ሕዝብ ሥቃይ ይይዛቸዋል።

15. የኤዶምም አለቆች ይርዳሉ፤የሞአብ አለቆች በእንቅጥቃጤ ይያዛሉ፤የከነዓን ሕዝብ ይቀልጣሉ።

16. አቤቱ እግዚአብሔር (ያህዌ) ሆይ፤ ሕዝብህእስከሚያልፉ ድረስ፣የተቤዠኻቸው ሕዝብህ እስኪያልፉ ድረስ፣ድንጋጤና ሽብር በእነርሱ ላይ ይመጣል፤በክንድህ ብርታት፣እንደ ድንጋይ የማይንቀሳቀሱ ይሆናሉ።

ዘፀአት 15