6. አንተ ለአምላክህ ለእግዚአብሔር (ኤሎሂም ያህዌ) ቅዱስ ሕዝብ ስለ ሆንህ፣ አምላክህ እግዚአብሔር (ኤሎሂም ያህዌ) የራሱ ሕዝብ፣ ርስትም እንድትሆንለት በምድር ላይ ከሚኖሩ ሕዝቦች ሁሉ መረጠህ።
7. እግዚአብሔር (ያህዌ) እናንተን የወደዳችሁና የመረጣችሁ ከሌሎች ሕዝቦች በቊጥር ስለ በዛችሁ አይደለም፤ ቊጥራችሁማ ከሕዝቦች ሁሉ እጅግ አነስተኛ ነበር።
8. ነገር ግን እናንተን በብርቱ እጅ ያወጣችሁ፣ ከባርነት ምድርና ከግብፅ ንጉሥ ከፈርዖን መዳፍ የተቤዣችሁ፣ እግዚአብሔር (ያህዌ) እናንተን ስለወደዳችሁና ለአባቶቻችሁ የማለላቸውን መሐላ ስለ ጠበቀ ነው።
9. ስለዚህም አምላክህ እግዚአብሔር (ኤሎሂም ያህዌ) አምላክ (ኤሎሂም) መሆኑን ዕወቅ፤ እርሱ ለሚወዱትና ትእዛዞቹን ለሚጠብቁት የፍቅሩን ኪዳን እስከ ሺህ ትውልድ ድረስ የሚጠብቅ ታማኝ አምላክ (ኤሎሂም) ነው።
10. ነገር ግን፣ የሚጠሉትን ዐይናቸው እያየ ይበቀላቸዋል፤ የሚጠሉትን ዐይናቸው እያየ ለመበቀል አይዘገይም።
11. ስለዚህ በዛሬው ቀን የምሰጥህን ትእዛዙን፣ ሥርዐቱንና ሕግጋቱን ለመከተል ጥንቃቄ አድርግ።
12. እነዚህን ሕግጋት ብታዳምጥና በጥንቃቄ ብትጠብቃቸው፣ አምላክህ እግዚአብሔር (ኤሎሂም ያህዌ) ለአባቶችህ እንደ ማለላቸው ከአንተ ጋር የገባውን የፍቅር ኪዳኑን ይጠብቃል።
13. ይወድሃል፤ ይባርክሃል፤ ያበዛሃልም። ለአንተ ለመስጠት ለአባቶችህ በማለላቸው ምድር የማሕፀንህን ፍሬ፣ የምድርህን ሰብል፣ እህልህን፣ አዲሱን ወይንና ዘይት፤ የከብት መንጋህን ጥጆች፣ የበግና የፍየል መንጋህን ግልገሎች ይባርካል።
14. ከሕዝቦች ሁሉ የበለጠ አንተ ትባረካለህ፤ ከአንተ ወይም ከከብቶችህ መካከል የማይወልድ ወንድ ወይም ሴት አይኖርም።
15. እግዚአብሔር (ያህዌ) ከማናቸውም በሽታ ነጻ ያደርግሃል፤ በግብፅ የምታውቃቸውን እነዚያን አሠቃቂ በሽታዎች በሚጠሉህ ሁሉ ላይ እንጂ በአንተ ላይ አያመጣብህም።
16. አምላክህእግዚአብሔር (ኤሎሂም ያህዌ) በእጅህ አሳልፎ የሚሰጥህን ሕዝቦች ሁሉ ማጥፋት አለብህ፤ አትዘንላቸው፤ ወጥመድ ስለሚሆኑብህም አማልክታቸውን አታምልክ።