ዘዳግም 6:8-16 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

8. በእጅህ ላይ ምልክት አድርገህ እሰራቸው፤ በግንባርህም ላይ ይሁኑ።

9. በቤትህ መቃኖች በግቢህም በሮች ላይ ጻፋቸው።

10. አምላክህ እግዚአብሔር (ኤሎሂም ያህዌ) ለአንተ ለመስጠት ለአባቶችህ ለአብርሃም፣ ለይስሐቅና ለያዕቆብ ወደ ማለላቸው ምድር ሲያስገባህ፣ በዚያም ያልሠራሃቸውን ታላላቅና ያማሩ ከተሞችን፣

11. የራስህ ባልነበሩ መልካም ነገሮች ሁሉ የተሞሉ ቤቶችን ያልቈፈርሃቸውን የውሃ ጒድጓዶች፣ ያልተከልሃቸውን የወይን ተክሎችና የወይራ ዛፎች ሲሰጥህና በልተህም ስትጠግብ፣

12. ከባርነት ምድር ከግብፅ ያወጣህን እግዚአብሔርን (ያህዌ) እንዳትረሳ ተጠንቀቅ!

13. አምላክህን እግዚአብሔርን (ኤሎሂም ያህዌ) ፍራ፤ እርሱን ብቻ አገልግል፤ በስሙም ማል።

14. በዙሪያህ ያሉ ሕዝቦች የሚያመልኳቸውን ሌሎች አማልክት አትከተል፤

15. ምክንያቱም በመካከልህ ያለው አምላክህ እግዚአብሔር (ኤሎሂም ያህዌ) ቀናተኛ አምላክ (ኤሎሂም) ስለ ሆነ፣ በአንተም ላይ ቊጣው ስለሚነድ፣ ከምድር ገጽ ያጠፋሃል።

16. በማሳህ እንዳደረጋችሁት አምላካችሁን እግዚአብሔርን (ኤሎሂም ያህዌ) አትፈታተኑት።

ዘዳግም 6