1. ዮርዳኖስን ተሻግራችሁ በምትወርሷት ምድር እንድትጠብቁት አስተምራችሁ ዘንድ አምላካችሁእግዚአብሔር (ኤሎሂም ያህዌ) የሰጠኝ ትእዛዝ፣ ሥርዐትና ሕግ ይህ ነው፤
2. ይኸውም፣ የምሰጣችሁን ሥርዐቱንና ትእዛዙን ሁሉ በመጠበቅ፣ ዕድሜያችሁ እንዲረዝም፣ አንተ፣ ልጆችህና ከእነርሱ በኋላ የሚመጡት ልጆቻቸው በሕይወት ዘመናችሁ ሁሉ አምላካችሁን እግዚአብሔርን (ኤሎሂም ያህዌ) ትፈሩት ዘንድ ነው።
3. እንግዲህ እስራኤል ሆይ ስማ፤ የአባቶችህ አምላክ እግዚአብሔር (ኤሎሂም ያህዌ) በሰጠህ ተስፋ መሠረት፣ ማርና ወተት በምታፈሰው ምድር መልካም እንዲሆንልህና እጅግ እንድትበዛ፣ ትእዛዙንም ትጠብቅ ዘንድ ጥንቃቄ አድርግ።
4. እስራኤል ሆይ ስማ፤ አምላካችንእግዚአብሔር (ኤሎሂም ያህዌ) አንድ እግዚአብሔር (ያህዌ) ነው።
5. አምላክህን እግዚአብሔርን (ኤሎሂም ያህዌ) በፍጹም ልብህ፣ በፍጹም ነፍስህ፣ በፍጹም ኀይልህ ውደድ።
6. ዛሬ የምሰጥህን እነዚህን ትእዛዛት በልብህ ያዝ።
7. ለልጆችህም አስጠናቸው፤ በቤትህ ስትቀመጥ፣ በመንገድም ስትሄድ፣ ስትተኛና ስትነሣም ስለ እነርሱ ተናገር።