15. በግብፅ ሳለህ አንተም ባሪያ እንደ ነበርህ፣ ከዚያም አምላክህ እግዚአብሔር (ኤሎሂም ያህዌ) በጸናች እጅና በተዘረጋ ክንድ እንዳወጣህ አስታውስ፤ ስለዚህ አምላክህእግዚአብሔር (ኤሎሂም ያህዌ) የሰንበትን ቀን ታከብረው ዘንድ አዘዘህ።
16. “አምላክህ እግዚአብሔር (ኤሎሂም ያህዌ) በሚሰጥህ ምድር ላይ ዕድሜህ እንዲረዝምና መልካም እንዲሆንልህ፣ አምላክህ እግዚአብሔር (ኤሎሂም ያህዌ) ባዘዘህ መሠረት አባትህንና እናትህን አክብር።
17. “አትግደል።
18. “አታመንዝር።
19. “አትስረቅ።
20. “በባልንጀራህ ላይ በሐሰት አትመስክር።
21. “የባልንጀራህን ሚስት አትመኝ። በባልንጀራህ ቤትም ሆነ በመሬቱ፣ በወንድ ሆነ በሴት አገልጋዩ፣ በበሬውም ሆነ በአህያው ወይም የእርሱ በሆነው ነገር ላይ ዐይንህን አትጣል።”
22. እግዚአብሔር (ያህዌ) በተራራው ላይ በእሳቱ፣ በደመናውና በድቅድቁ ጨለማ ውስጥ ለማኅበራችሁ ሁሉ በከፍተኛ ድምፅ የተናገራችሁ ትእዛዛቱ እነዚህ ናቸው፤ የጨመረውም ሌላ የለም፤ ትእዛዛቱንም በሁለት የድንጋይ ጽላቶች ላይ ጽፎ ሰጠኝ።
23. ተራራው በእሳት ሲቃጠል፣ ከጨለማው ውስጥ ድምፁን በሰማችሁ ጊዜ እናንተ የየነገዶቻችሁ አለቆችና ሽማግሌዎቻችሁም በሙሉ ወደ እኔ ዘንድ መጣችሁ፤