14. ሰባተኛው ቀን ግን የአምላክህ የእግዚአብሔር (ኤሎሂም ያህዌ) ሰንበት ነው። በዚህም ቀን አንተም ሆንህ ወንድ ወይም ሴት ልጅህ፣ ወንድ አገልጋይህም ሆነ ሴት አገልጋይህ በሬህ፣ አህያህ ወይም ማናቸውም እንሰሳህ፣ ወይም ደግሞ በደጅህ ያለ እንግዳ ምንም ዐይነት ሥራ አትሥሩ። ይህም አንተ እንዳረፍህ ሁሉ ወንድ አገልጋይህም ሆነ ሴት አገልጋይህ እንዲያርፉ ነው።
15. በግብፅ ሳለህ አንተም ባሪያ እንደ ነበርህ፣ ከዚያም አምላክህ እግዚአብሔር (ኤሎሂም ያህዌ) በጸናች እጅና በተዘረጋ ክንድ እንዳወጣህ አስታውስ፤ ስለዚህ አምላክህእግዚአብሔር (ኤሎሂም ያህዌ) የሰንበትን ቀን ታከብረው ዘንድ አዘዘህ።
16. “አምላክህ እግዚአብሔር (ኤሎሂም ያህዌ) በሚሰጥህ ምድር ላይ ዕድሜህ እንዲረዝምና መልካም እንዲሆንልህ፣ አምላክህ እግዚአብሔር (ኤሎሂም ያህዌ) ባዘዘህ መሠረት አባትህንና እናትህን አክብር።
17. “አትግደል።
18. “አታመንዝር።
19. “አትስረቅ።
20. “በባልንጀራህ ላይ በሐሰት አትመስክር።
21. “የባልንጀራህን ሚስት አትመኝ። በባልንጀራህ ቤትም ሆነ በመሬቱ፣ በወንድ ሆነ በሴት አገልጋዩ፣ በበሬውም ሆነ በአህያው ወይም የእርሱ በሆነው ነገር ላይ ዐይንህን አትጣል።”
22. እግዚአብሔር (ያህዌ) በተራራው ላይ በእሳቱ፣ በደመናውና በድቅድቁ ጨለማ ውስጥ ለማኅበራችሁ ሁሉ በከፍተኛ ድምፅ የተናገራችሁ ትእዛዛቱ እነዚህ ናቸው፤ የጨመረውም ሌላ የለም፤ ትእዛዛቱንም በሁለት የድንጋይ ጽላቶች ላይ ጽፎ ሰጠኝ።
23. ተራራው በእሳት ሲቃጠል፣ ከጨለማው ውስጥ ድምፁን በሰማችሁ ጊዜ እናንተ የየነገዶቻችሁ አለቆችና ሽማግሌዎቻችሁም በሙሉ ወደ እኔ ዘንድ መጣችሁ፤
24. እንዲህም አላችሁ፤ “አምላካችን እግዚአብሔር (ኤሎሂም ያህዌ) ክብሩንና ግርማውን አሳይቶናል፤ ከእሳቱም ውስጥ ድምፁን ሰምተናል። እግዚአብሔር አነጋግሮትም እንኳ፣ ሰው በሕይወት ሊኖር እንደሚችል በዛሬው ቀን አይተናል።
25. ከእንግዲህ የአምላካችንን የእግዚአብሔርን (ኤሎሂም ያህዌ) ድምፅ ብንሰማ እንሞታለን፤ ይህችም ታላቅ እሳት ፈጽማ ታጠፋናለች፤ ታዲያ ለምን እንሙት?
26. ለመሆኑ ከእሳት ውስጥ ሆኖ ሲናገር እኛ እንደ ሰማነው ሁሉ፣ የሕያው እግዚአብሔርን (ኤሎሂም) ድምፅ ሰምቶ በሕይወት ለመኖር የቻለ ከሥጋ ለባሽ ማን አለ?
27. አንተ ቅረብ፤ አምላካችን እግዚአብሔር (ኤሎሂም ያህዌ) የሚለውን ሁሉ አዳምጥ፤ ከዚያም አምላካችን እግዚአብሔር (ኤሎሂም ያህዌ) የሚነግርህን ሁሉ ንገረን፤ እኛም እንሰማለን፤ እናደርገዋለንም።”
28. ይህን ስትነግሩኝ እግዚአብሔር (ያህዌ) ሰማ፤ እግዚአብሔርም (ያህዌ) አለኝ፤ “ይህ ሕዝብ ምን እንዳለህ ሰምቻለሁ፤ ያሉትም ሁሉ መልካም ነው።
29. ታዲያ ለእነርሱም ሆነ ለልጆቻቸው ለዘላለም መልካም እንዲሆንላቸው፣ እኔን እንዲፈሩና ሁል ጊዜ ትእዛዞቼን ሁሉ እንዲጠብቁ እንደዚህ ያለ ልብ ቢኖራቸው ምናለ!
30. ሄደህ ወደየድንኳናቸው እንዲመለሱ ንገራቸው።