ዘዳግም 4:34-46 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

34. አምላካችሁ እግዚአብሔር (ኤሎሂም ያህዌ) በዐይናችሁ እያያችሁ ለእናንተ በግብፅ እንዳደረገው ሁሉ በፈተና፣ በታምራዊ ምልክቶችና በድንቆች፣ በጦርነት፣ በጸናች እጅና በተዘረጋች ክንድ ወይም በታላቅና በአስፈሪ ሥራዎች ከሌላ ሕዝብ መካከል አንድን ሕዝብ የራሱ ለማድረግ የቻለ አምላክ አለን?

35. እግዚአብሔር እርሱ አምላክ (ያህዌ ኤሎሂም) መሆኑን፣ ከእርሱም በቀር ሌላ አምላክ አለመኖሩን ታውቁ ዘንድ እነዚህን ነገሮች እንድታዩ ተደረገ።

36. ሊገሥጽህ ድምፁን ከሰማይ እንድትሰማ አደረገ፤ በምድርም ላይ አስፈሪ እሳቱን አሳየህ፤ ከእሳቱም ውስጥ ቃሉን ሰማህ።

37. አባቶችህን ከመውደዱ የተነሣና ከእነርሱም በኋላ ዘራቸውን ስለ መረጠ፣ ከአንተ ጋር በመሆን በታላቅ ኀይሉ ከግብፅ አወጣህ፤

38. ዛሬ እንደሆነው ሁሉ ከአንተ ይልቅ ታላቅና ብርቱ የሆኑትን አሕዛብ ከፊትህ በማስወጣት ወደ ምድራቸው አስገብቶህ ለአንተ ርስት አድርጎ ለመስጠት ነው።

39. እንግዲህ በላይ በሰማይ፣ በታችም በምድር እግዚአብሔር እርሱ አምላክ (ያህዌ ኤሎሂም) መሆኑን ዛሬ ዕወቅ፤ በልብህም ያዘው፤ ሌላም የለም።

40. ለአንተና ከአንተም በኋላ ለልጆችህ መልካም እንዲሆንላችሁ፣ አምላክህ እግዚአብሔር (ኤሎሂም ያህዌ) ለዘላለም በሚሰጥህም ምድር ዕድሜህ እንዲረዝም፣ ዛሬ እኔ የማዝህን ሥርዐቱንና ሕግጋቱን ጠብቅ።

41. በዚያን ጊዜ ሙሴ ከዮርዳኖስ በስተ ምሥራቅ ሦስት ከተሞችን ለየ፤

42. ይኸውም የቈየ ጠላትነት ሳይኖር፣ በድንገት ባልንጀራውን የገደለ ማናቸውም ሰው ሸሽቶ ከእነዚህ ከተሞች ወደ አንዲቱ በመሄድ ሕይወቱን ማትረፍ ይችል ዘንድ ነው።

43. ከተሞቹም በምድረ በዳው በከፍተኛ ቦታ ላይ የምትገኘው ቦሶር ለሮቤላውያን፣ በገለዓድ የምትገኘው ራሞት ለጋዳውያን፣ በባሳን ያለችው ጎላን ለምናሴያውያን ነበሩ።

44. ሙሴ በእስራኤላውያን ፊት የደነገገው ሕግ ይህ ነው።

45. ከግብፅ በወጡ ጊዜ ሙሴ ለእስራኤላውያን የሰጣቸው መመሪያዎች፣ ሥርዐቶችና ሕጎች እነዚህ ናቸው፤

46. ይህም ከግብፅ በወጡ ጊዜ በሙሴና በእስራኤላውያን ድል በተደረገው፣ በሐሴቦን በነገሠው፣ በአሞራውያን ንጉሥ በሴዎን ምድር፣ ከዮርዳኖስ በስተ ምሥራቅ በቤተ ፌጎር አጠገብ ባለው ሸለቆ ውስጥ በነበሩበት ጊዜ ነው።

ዘዳግም 4