ዘዳግም 4:3-19 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

3. እግዚአብሔር (ያህዌ) በብዔልፌጎር ላይ ምን እንዳደረገ በዐይናችሁ አይታችኋል፤ አምላካችሁ እግዚአብሔር (ኤሎሂም ያህዌ) ከመካከላችሁ ብዔልፌጎርን የተከተሉትን ሁሉ አጥፍቶአቸዋል፤

4. አምላካችሁን እግዚአብሔርን (ኤሎሂም ያህዌ) የተከተላችሁት እናንተ ሁላችሁ ግን ይኸው እስከ ዛሬ በሕይወት አላችሁ።

5. ገብታችሁ በምትወርሷት ምድር፣ እንድትፈጽሟቸው እግዚአብሔር አምላኬ (ያህዌ ኤሎሂም) ባዘዘኝ መሠረት ሥርዐትንና ሕግን አስተምሬአችኋለሁ።

6. በጥንቃቄ ጠብቋቸው፤ ስለ እነዚህ ሥርዐቶች ሁሉ ለሚሰሙና፣ “በእውነቱ ይህ ታላቅ ሕዝብ የቱን ያህል ጥበበኛና አስተዋይ ነው” ለሚሉ ሕዝቦች ይህ ጥበባችሁንና ማስተዋላችሁን ይገልጣልና።

7. በምንጠራው ጊዜ ሁሉ አምላካችን እግዚአብሔር (ኤሎሂም ያህዌ) ለእኛ ቅርብ እንደሆነ አማልክቱ የሚቀርቡት ሌላ ታላቅ ሕዝብ ማነው?

8. ዛሬ እኔ በፊታችሁ እንዳስቀመጥሁት ሕግ ያለ ጽድቅ የሆነ ሥርዐትና ሕግ ያሉት ሌላ ታላቅ ሕዝብስ ማነው?

9. ዐይኖቻችሁ ያዩዋቸውን ነገሮች እንዳትረሱ፣ ደግሞም በሕይወት እስካላችሁ ድረስ ከልባችሁ እንዳይጠፉ ብቻ ተጠንቀቁ፣ ነቅታችሁም ራሳችሁን ጠብቁ። እነዚህን ለልጆቻችሁና ከእነርሱ በኋላ ለሚወለዱት ልጆቻቸው አስተምሯቸው።

10. “በምድሪቱ በሚኖሩበት ጊዜ ሁሉ እኔን ማክበር እንዲማሩ፣ ለልጆቻቸውም እንዲያስተምሩ ቃሌን ይሰሙ ዘንድ ሕዝቡን በፊቴ ሰብስብ” ባለኝ ጊዜ፣ በኮሬብ በአምላካችሁ በእግዚአብሔር (ኤሎሂም ያህዌ) ፊት የቆማችሁበትን ዕለት አስታውሱ።

11. ተራራው በጥቍር ደመናና በድቅድቅ ጨለማ ተውጦ ሳለ ነበልባሉ ሰማይ እስከሚደርስ ድረስ በተቃጠለ ጊዜ መጥታችሁ ከተራራው ግርጌ ቆማችሁ።

12. ከዚያም እግዚአብሔር (ያህዌ) በእሳቱ ውስጥ ሆኖ ተናገራችሁ፤ እናንተም የቃሉን ድምፅ ሰማችሁ፤ መልክ ግን አላያችሁም፤ ድምፅ ብቻ ነበርና።

13. እርሱ ኪዳኑን ይኸውም እንድትከተሏቸው ያዘዛችሁን ዐሠርቱን ትእዛዛት ዐወጀላችሁ፤ ከዚያም በሁለት የድንጋይ ጽላቶች ላይ ጻፋቸው፤

14. ዮርዳኖስን ተሻግራችሁ በምትወርሷት ምድር ውስጥ የምትከተሏቸውን ሥርዐትና ሕግ እንዳስ ተምራችሁ በዚያን ጊዜ እግዚአብሔር (ያህዌ) አዘዘኝ።

15. እግዚአብሔር (ያህዌ) በኮሬብ ተራራ ላይ በእሳት ውስጥ በተናገራችሁ ቀን ምንም ዐይነት መልክ ከቶ አላያችሁም፤ ስለዚህ ለራሳችሁ ተጠንቀቁ፤

16. ይኸውም እንዳትረክሱ፣ በወንድ ወይም በሴት መልክ በማናቸውም ዐይነት ምስል የተቀረጸ ጣዖት ለራሳችሁ እንዳታበጁ፣

17. ወይም በምድር ላይ የሚኖር የማናቸውንም እንስሳ ወይም በአየር ላይ የሚበር የማናቸውንም ወፍ፣

18. ወይም በደረቱ የሚሳብ የማናቸውንም ፍጡር ወይም በውሃ ውስጥ የሚኖር የማናቸውንም ዓሣ ምስል እንዳታደርጉ ነው።

19. ወደ ሰማይ ቀና ብለህ ፀሓይን፣ ጨረቃንና ከዋክብትን፣ የሰማይ ሰራዊትንም ሁሉ በምትመለከትበት ጊዜ፣ ወደ እነርሱ እንዳትሳብና እንዳትሰግድላቸው፣ አምላክህ እግዚአብሔር (ኤሎሂም ያህዌ) ከሰማይ በታች ላሉ ሕዝቦች ሁሉ ድርሻ አድርጎ የሰጣቸውንም ነገሮች እንዳታመልክ ተጠንቀቅ፤

ዘዳግም 4