ዘዳግም 4:10-30 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

10. “በምድሪቱ በሚኖሩበት ጊዜ ሁሉ እኔን ማክበር እንዲማሩ፣ ለልጆቻቸውም እንዲያስተምሩ ቃሌን ይሰሙ ዘንድ ሕዝቡን በፊቴ ሰብስብ” ባለኝ ጊዜ፣ በኮሬብ በአምላካችሁ በእግዚአብሔር (ኤሎሂም ያህዌ) ፊት የቆማችሁበትን ዕለት አስታውሱ።

11. ተራራው በጥቍር ደመናና በድቅድቅ ጨለማ ተውጦ ሳለ ነበልባሉ ሰማይ እስከሚደርስ ድረስ በተቃጠለ ጊዜ መጥታችሁ ከተራራው ግርጌ ቆማችሁ።

12. ከዚያም እግዚአብሔር (ያህዌ) በእሳቱ ውስጥ ሆኖ ተናገራችሁ፤ እናንተም የቃሉን ድምፅ ሰማችሁ፤ መልክ ግን አላያችሁም፤ ድምፅ ብቻ ነበርና።

13. እርሱ ኪዳኑን ይኸውም እንድትከተሏቸው ያዘዛችሁን ዐሠርቱን ትእዛዛት ዐወጀላችሁ፤ ከዚያም በሁለት የድንጋይ ጽላቶች ላይ ጻፋቸው፤

14. ዮርዳኖስን ተሻግራችሁ በምትወርሷት ምድር ውስጥ የምትከተሏቸውን ሥርዐትና ሕግ እንዳስ ተምራችሁ በዚያን ጊዜ እግዚአብሔር (ያህዌ) አዘዘኝ።

15. እግዚአብሔር (ያህዌ) በኮሬብ ተራራ ላይ በእሳት ውስጥ በተናገራችሁ ቀን ምንም ዐይነት መልክ ከቶ አላያችሁም፤ ስለዚህ ለራሳችሁ ተጠንቀቁ፤

16. ይኸውም እንዳትረክሱ፣ በወንድ ወይም በሴት መልክ በማናቸውም ዐይነት ምስል የተቀረጸ ጣዖት ለራሳችሁ እንዳታበጁ፣

17. ወይም በምድር ላይ የሚኖር የማናቸውንም እንስሳ ወይም በአየር ላይ የሚበር የማናቸውንም ወፍ፣

18. ወይም በደረቱ የሚሳብ የማናቸውንም ፍጡር ወይም በውሃ ውስጥ የሚኖር የማናቸውንም ዓሣ ምስል እንዳታደርጉ ነው።

19. ወደ ሰማይ ቀና ብለህ ፀሓይን፣ ጨረቃንና ከዋክብትን፣ የሰማይ ሰራዊትንም ሁሉ በምትመለከትበት ጊዜ፣ ወደ እነርሱ እንዳትሳብና እንዳትሰግድላቸው፣ አምላክህ እግዚአብሔር (ኤሎሂም ያህዌ) ከሰማይ በታች ላሉ ሕዝቦች ሁሉ ድርሻ አድርጎ የሰጣቸውንም ነገሮች እንዳታመልክ ተጠንቀቅ፤

20. እናንተን ግን ልክ ዛሬ እንደሆናችሁት ሁሉ ርስቱ ትሆኑለት ዘንድ፣ አምላካችሁ እግዚአብሔር (ኤሎሂም ያህዌ) እናንተን ከብረት ማቅለጫ ምድጃ፣ ከግብፅ አውጥቶ አመጣችሁ።

21. በእናንተም ምክንያት እግዚአብሔር እኔን ተቈጣኝ፤ ዮርዳኖስንም እንዳልሻገርና አምላካችሁ እግዚአብሔር (ኤሎሂም ያህዌ) ርስት አድርጎ ወደሚሰጣችሁ ወደ መልካሚቱ ምድር እንዳልገባ ማለ።

22. እኔም በዚህች ምድር እሞታለሁ፤ ዮርዳኖስን አልሻገርም፤ እናንተ ግን ልትሻገሩ ነው፤ ያችንም መልካም ምድር ትወርሳላችሁ።

23. አምላካችሁእግዚአብሔር (ኤሎሂም ያህዌ) ከእናንተ ጋር የገባውን ኪዳን እንዳትረሱ ተጠንቀቁ፤ አምላካችሁ እግዚአብሔር (ኤሎሂም ያህዌ) የከለከለውን ጣዖት በማናቸውም ዐይነት መልክ ለራሳችሁ አታብጁ።

24. አምላካችሁ እግዚአብሔር (ኤሎሂም ያህዌ) የሚባላ እሳት ቀናተኛም አምላክ (ኤሎሂም) ነውና።

25. ልጆችንና የልጅ ልጆችን ከወለዳችሁና በምድሪቱም ላይ ለረጅም ጊዜ ከኖራችሁ በኋላ ራሳችሁን በማርከስ ማንኛውንም ዐይነት ጣዖት ብታበጁ፣ በአምላካችሁም በእግዚአብሔር (ኤሎሂም ያህዌ) ፊት ክፋት በማድረግ ለቊጣ ብታነሣሡት፣

26. ዮርዳኖስን ተሻግራችሁ ከምትወርሷት ምድር ላይ ፈጥናችሁ እንደምትጠፉ በዚህ ቀን ሰማይንና ምድርን በእናንተ ላይ ምስክሮች አድርጌ እጠራለሁ፣ በዚያ ቦታ ብዙ ዘመን አትኖሩም፤ ፈጽሞ ትጠፋላችሁ።

27. እግዚአብሔር (ያህዌ) እናንተን በአሕዛብ መካከል ይበትናችኋል፤ እግዚአብሔር በሚበትናችሁ አሕዛብ መካከል የምትተርፉት ጥቂቶቻችሁ ብቻ ናችሁ።

28. እዚያም፣ ማየት ወይም መስማት ወይም መብላት ወይም ማሽተት በማይችሉ በሰው እጅ በተሠሩ የዕንጨትና የድንጋይ አማልክት ታመልካላችሁ።

29. ነገር ግን እዚያም ሆናችሁ አምላካችሁን እግዚአብሔርን (ኤሎሂም ያህዌ) በፍጹም ልባችሁና በፍጹም ነፍሳችሁ ብትፈልጉት ታገኙታላችሁ።

30. ስትጨነቅና ይህ ሁሉ ነገር ሲደርስብህ ያን ጊዜ፣ በኋለኞቹ ዘመናት ወደ አምላክህ ወደ እግዚአብሔር (ኤሎሂም ያህዌ) ትመለሳለህ፤ ትታዘዝለታለህም።

ዘዳግም 4