ዘዳግም 32:36-46 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

36. ኀይላቸው መድከሙን፣ባሪያም ሆነ ነጻ ሰው አለመቅረቱን በሚያይበት ጊዜ፣ እግዚአብሔር (ያህዌ) ለሕዝቡ ይፈርዳል፤ለአገልጋዮቹም ይራራል።

37. እንዲህም ይላል፤ “መጠጊያ ዐለት የሆኗቸው፣እነዚያ አማልክታቸው የት አሉ?

38. የመሥዋዕታቸውን ስብ የበሉ፣የመጠጥ ቊርባናቸውንም የወይን ጠጅ የጠጡ አማልክት ወዴት ናቸው?እስቲ ይነሡና ይርዷችሁ!እስቲ መጠለያ ይስጧችሁ!

39. “እኔ ራሴ እርሱ እንደሆንሁ እዩ፤ከእኔም በቀር ሌላ አምላክ የለም፤እገድላለሁ፤ አድናለሁም፤አቈስላለሁ፤ እፈውሳለሁም፤ከእጄም የሚያስጥል ማንም የለም።

40. እጄን ወደ ሰማይ አነሣለሁ፤ለዘላለምም ሕያው እንደሆንሁ እናገራለሁ፤

41. የሚያብረቀርቅ ሰይፌን ስዬ፣እጄ ለፍርድ ስትይዘው፣ባላጋራዎቼን እበቀላቸዋለሁ፤የሚጠሉኝንም እንደ ሥራቸው እከፍላቸዋለሁ።

42. ሰይፌ ሥጋ በሚበላበት ጊዜ፣ፍላጾቼ በደም እንዲሰክሩ አደርጋለሁ፤ደሙ የታረዱትና የምርኮኞች፣የጠላት አለቆችም ራስ ደም ነው።”

43. አሕዛብ ሆይ፤ ከሕዝቡ ጋር ደስ ይበላችሁ፤እርሱ የአገልጋዮቹን ደም ይመልሳል፤ጠላቶቹንም ይበቀላል።ምድሪቱንና ሕዝቡን ይቤዣቸዋልና።

44. ሙሴም ከነዌ ልጅ ከኢያሱ ጋር መጥቶ የዚህን መዝሙር ቃሎች በሕዝቡ ጆሮ ተናገረ።

45. ሙሴም እነዚህን ቃሎች ሁሉ ለመላው እስራኤል ተናግሮ ከጨረሰ በኋላ፣

46. እንዲህ አላቸው፤ የዚህን ሕግ ቃሎች ሁሉ በጥንቃቄ ይጠብቁ ዘንድ ልጆቻችሁን እንድታዟቸው፣ እኔ ዛሬ በግልጥ የምነግራችሁን ቃሎች ሁሉ በልባችሁ አኑሩ።

ዘዳግም 32