ዘዳግም 28:38-53 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

38. በዕርሻ ላይ ብዙ ዘር ትዘራለህ፤ አንበጣ ስለሚበላው የምትሰበስበው ጥቂት ይሆናል።

39. ወይን ትተክላለህ፤ ትንከባከበዋለህ፤ ነገር ግን ዘለላውን አትሰበስብም።

40. በአገርህ ምድር ሁሉ የወይራ ዛፍ ይኖርሃል፤ ፍሬው ስለሚረግፍብህ ግን ዘይቱን አትጠቀምበትም።

41. ወንዶችና ሴቶች ልጆች ትወልዳለህ፤ ነገር ግን በምርኮ ስለሚወሰዱ፣ አብረውህ አይኖሩም።

42. ዛፍህንና የምድርህን ሰብል ሁሉ የአንበጣ መንጋ ይወረዋል።

43. በመካከልህ የሚኖር መጻተኛ ከአንተ በላይ ከፍ ከፍ ሲል አንተ ግን ዝቅ ዝቅ ትላለህ።

44. እርሱ ያበድርሃል እንጂ አንተ አታበድረውም። እርሱ ራስ ይሆናል፤ አንተ ግን ጅራት ትሆናለህ።

45. እነዚህ ርግማኖች ሁሉ በአንተ ላይ ይመጣሉ፤ አምላክህን እግዚአብሔርን (ኤሎሂም ያህዌ) ስላል ታዘዝህና የሰጠህን ትእዛዝና ሥርዐት ስላልጠበቅህ እስክትጠፋ ድረስ ይከተሉሃል፤ ይወርዱብሃልም።

46. ለአንተና ለዘርህ ለዘላለም ምልክትና መገረም ይሆናሉ።

47. በብልጽግና ጊዜ አምላክህን እግዚአብሔርን (ኤሎሂም ያህዌ) በደስታና በሐሤት ስላላገለገልኸው፣

48. በራብና በጥም፣ በእርዛትና በከፋ ድኽነት እግዚአብሔር (ያህዌ) የሚያስነሣብህን ጠላቶችህን ታገለግላለህ፤ እስኪያጠፋህም ድረስ በዐንገትህ ላይ የብረት ቀንበር ይጭንብሃል።

49. እግዚአብሔር (ያህዌ) እንደ ንስር ፈጥኖ የሚወርድንና ቋንቋውን የማታውቀውን ሕዝብ እጅግ ሩቅ ከሆነ፣ ከምድርም ዳርቻ ያሰነሣብሃል፤

50. ሽማግሌ የማያከብር፣ ለብላቴና የማይራራ፣ ሲያዩት የሚያስፈራ ሕዝብ ነው።

51. እስክትጠፋም ድረስ የእንስሳትህን ግልገልና የምድርህን ሰብል ይበላል፤ እስኪያጠፋህም ድረስ እህል፣ አዲስ የወይን ጠጅ ሆነ ዘይት፣ የመንጋህን ጥጃ ሆነ፣ የበግና ፍየል መንጋህን ግልገል አያስቀርልህም።

52. የምትታመንባቸውን ታላላቅ የተመሸጉ ቅጥሮች እስኪወድቁ ድረስ በመላው አገርህ ያሉትን ከተሞችህን ሁሉ ይከባል፤ አምላክህ እግዚአብሔር (ኤሎሂም ያህዌ) በሚሰጥህ ምድር ያሉትን ከተሞች በሙሉ ይወራቸዋል።

53. ጠላቶችህ ከበው በሚያስጨንቁህ ጊዜ፣ ከሥቃይ የተነሣ፣ አምላክህ እግዚአብሔር (ኤሎሂም ያህዌ) የሰጠህን፣ የወገብህ ፍሬ የሆኑትን የወንዶችና የሴቶች ልጆችህን ሥጋ ትበላለህ።

ዘዳግም 28