ዘዳግም 28:31-44 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

31. በሬህ ዐይንህ እያየ ይታረዳል፤ ከሥጋውም አንዳች አትቀምስም። አህያህም በግድ ይወሰድብሃል፤ አይመለስልህም። በጎችህ ለጠላቶችህ ይሰጣሉ፤ የሚያስጥላቸውም አይኖርም።

32. ወንዶችና ሴቶች ልጆችህ ለባዕድ ሕዝብ ይሰጣሉ፤ እጅህንም ለማንሣት ዐቅም ታጣለህ፤ ከዛሬ ነገ ይመጣሉ፤ በማለትም ዐይኖችህ ሁል ጊዜ እነርሱን በመጠባበቅ ይደክማሉ።

33. የምድርህንና የድካምህን ፍሬ ሁሉ የማታውቀው ሕዝብ ይበላዋል፤ ዕድሜ ልክህን በጭካኔና በጭቈና ከመኖር በቀር የሚተርፍህ ነገር አይኖርም።

34. የምታየው ሁሉ ያሳብድሃል።

35. እግዚአብሔር (ያህዌ) ከእግርህ ጥፍር እስከ ራስህ ጠጒር በሚዛመት፣ ሊድን በማይችልና በሚያሠቃይ ቊስል ጒልበትህንና እግርህን ይመታሃል።

36. እግዚአብሔር (ያህዌ) አንተንና በላይህ ያነገሥኸውን ንጉሥ፣ አንተና አባቶችህ ወደማታውቁት ሕዝብ ይወስዳችኋል፤ ከዚያም ከዕንጨትና ከድንጋይ የተሠሩ ሌሎች አማልክትን ታመልካለህ።

37. እግዚአብሔር (ያህዌ) እንድትገባ በሚያደርግበት ምድር ለአሕዛብ ሁሉ መሸማቀቂያ፣ ማላገጫና መዘባበቻ ትሆናለህ።

38. በዕርሻ ላይ ብዙ ዘር ትዘራለህ፤ አንበጣ ስለሚበላው የምትሰበስበው ጥቂት ይሆናል።

39. ወይን ትተክላለህ፤ ትንከባከበዋለህ፤ ነገር ግን ዘለላውን አትሰበስብም።

40. በአገርህ ምድር ሁሉ የወይራ ዛፍ ይኖርሃል፤ ፍሬው ስለሚረግፍብህ ግን ዘይቱን አትጠቀምበትም።

41. ወንዶችና ሴቶች ልጆች ትወልዳለህ፤ ነገር ግን በምርኮ ስለሚወሰዱ፣ አብረውህ አይኖሩም።

42. ዛፍህንና የምድርህን ሰብል ሁሉ የአንበጣ መንጋ ይወረዋል።

43. በመካከልህ የሚኖር መጻተኛ ከአንተ በላይ ከፍ ከፍ ሲል አንተ ግን ዝቅ ዝቅ ትላለህ።

44. እርሱ ያበድርሃል እንጂ አንተ አታበድረውም። እርሱ ራስ ይሆናል፤ አንተ ግን ጅራት ትሆናለህ።

ዘዳግም 28