ዘዳግም 28:1-8 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

1. ለአምላክህ ለእግዚአብሔር (ኤሎሂም ያህዌ) በፍጹም ብትታዘዝና እኔ ዛሬ የምሰጥህን ትእዛዙን ሁሉ በጥንቃቄ ብትከተል፣ አምላክህ እግዚአብሔር (ኤሎሂም ያህዌ) በምድር ላይ ከሚኖሩ አሕዛብ ሁሉ በላይ ከፍ ያደርግሃል።

2. አምላክህን እግዚአብሔርን (ኤሎሂም ያህዌ) ብትታዘዝ፣ እነዚህ በረከቶች ሁሉ ያንተ ይሆናሉ፤ አይለዩህምም።

3. በከተማ ትባረካለህ፣ በዕርሻህም ትባረካለህ።

4. የማሕፀንህ ፍሬ፣ የምድርህ አዝመራ፣ የእንስሳትህ ግልገሎች፣ የከብትህ ጥጃ፣ የበግና የፍየል ግልገሎችህም ይባረካሉ።

5. እንቅብህና ቡሓቃህ ይባረካሉ።

6. ስትገባ ትባረካለህ፤ ስትወጣም ትባረካለህ።

7. እግዚአብሔር (ያህዌ) በአንተ ላይ የሚነሡ ጠላቶችህን በፊትህ እንዲሸነፉ ያደርጋቸዋል፤ በአንድ አቅጣጫ ይመጡብሃል፤ በሰባት አቅጣጫም ከአንተ ይሸሻሉ።

8. እግዚአብሔር (ያህዌ) በጐተራህና እጅህ በነካው ሁሉ በረከቱን ይልካል። አምላክህ እግዚአብሔር (ኤሎሂም ያህዌ) በሚሰጥህም ምድር ላይ ይባርክሃል።

ዘዳግም 28