1. ለአምላክህ ለእግዚአብሔር (ኤሎሂም ያህዌ) በፍጹም ብትታዘዝና እኔ ዛሬ የምሰጥህን ትእዛዙን ሁሉ በጥንቃቄ ብትከተል፣ አምላክህ እግዚአብሔር (ኤሎሂም ያህዌ) በምድር ላይ ከሚኖሩ አሕዛብ ሁሉ በላይ ከፍ ያደርግሃል።
2. አምላክህን እግዚአብሔርን (ኤሎሂም ያህዌ) ብትታዘዝ፣ እነዚህ በረከቶች ሁሉ ያንተ ይሆናሉ፤ አይለዩህምም።
3. በከተማ ትባረካለህ፣ በዕርሻህም ትባረካለህ።
4. የማሕፀንህ ፍሬ፣ የምድርህ አዝመራ፣ የእንስሳትህ ግልገሎች፣ የከብትህ ጥጃ፣ የበግና የፍየል ግልገሎችህም ይባረካሉ።
5. እንቅብህና ቡሓቃህ ይባረካሉ።
6. ስትገባ ትባረካለህ፤ ስትወጣም ትባረካለህ።
7. እግዚአብሔር (ያህዌ) በአንተ ላይ የሚነሡ ጠላቶችህን በፊትህ እንዲሸነፉ ያደርጋቸዋል፤ በአንድ አቅጣጫ ይመጡብሃል፤ በሰባት አቅጣጫም ከአንተ ይሸሻሉ።
8. እግዚአብሔር (ያህዌ) በጐተራህና እጅህ በነካው ሁሉ በረከቱን ይልካል። አምላክህ እግዚአብሔር (ኤሎሂም ያህዌ) በሚሰጥህም ምድር ላይ ይባርክሃል።
9. የአምላክህን የእግዚአብሔርን (ኤሎሂም ያህዌ) ትእዛዞች የምትጠብቅና በመንገዱ የምትሄድ ከሆነ፣ በመሐላ በሰጠህ ተስፋ መሠረት የተቀደሰ ሕዝቡ አድርጎ ያቆምሃል፤
10. ከዚያም የምድር አሕዛብ ሁሉ በእግዚአብሔር (ያህዌ) ስም መጠራትህን ያያሉ፤ ይፈሩሃልም።
11. እግዚአብሔርም (ያህዌ) ሊሰጥህ ለአባቶችህ በማለላቸው ምድር በማሕፀንህ ፍሬ፣ በእንስሳትህም ግልገል፣ በምድርህም ሰብል የተትረፈረፈ ብልጽግና ይሰጥሃል።
12. እግዚአብሔር (ያህዌ) ለምድርህ በወቅቱ ዝናብን ለመስጠትና የእጅህን ሥራ ሁሉ ለመባረክ፣ መልካሙን መዝገብ ሰማዩን ይከፍትልሃል፤ አንተም ለብዙ አሕዛብ ታበድራለህ እንጂ ከአንዳቸውም አትበደርም።
13. እግዚአብሔርም (ያህዌ) ራስ እንጂ ጅራት አያደርግህም። ዛሬ የምሰጥህን የአምላክህንየእግዚአብሔርን (ኤሎሂም ያህዌ) ትእዛዝ በጥንቃቄ ብትጠብቅ መቼውንም ቢሆን እላይ እንጂ ፈጽሞ እታች አትሆንም።