ዘዳግም 27:9-19 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

9. ሙሴና ሌዋውያን ካህናትም ለእስራኤል ሁሉ እንዲህ አሉ፤ “እስራኤል ሆይ፤ ጸጥ ብለህ አድምጥ! አንተ ዛሬ የአምላክህ የእግዚአብሔር (ኤሎሂም ያህዌ) ሕዝብ ሆነሃል፤

10. አምላክህን እግዚአብሔርን (ኤሎሂም ያህዌ) ታዘዝ፤ ዛሬ የምሰጥህን ትእዛዙንና ሥርዐቱን ጠብቅ።”

11. ሙሴ በዚያኑ ዕለት ሕዝቡን እንዲህ ብሎ አዘዘ፦

12. ዮርዳኖስን በተሻገራችሁ ጊዜ፣ ስምዖን፣ ሌዊ፣ ይሁዳ፣ ይሳኮር፣ ዮሴፍና ብንያም ሕዝቡን ለመባረክ በገሪዛን ተራራ ላይ ይቁሙ።

13. ሮቤል፣ ጋድ፣ አሴር፣ ዛብሎን፣ ዳንና ንፍታሌምም በጌባል ተራራ ላይ ለመርገም ይቁሙ።

14. ሌዋውያን ድምፃቸውን ከፍ አድርገው ለእስራኤል ሕዝብ ሁሉ እንዲህ ብለው ይናገሩ፦

15. “የእጅ ጥበብ ባለ ሙያ የሠራውን፣ በእግዘአብሔር (ያህዌ) ዘንድ አስጸያፊ የሆነውን ምስል የሚቀርጽ ወይም ጣዖትን የሚያበጅ፣ በስውርም የሚያቆም ሰው የተረገመ ይሁን።”ሕዝቡም ሁሉ፣ “አሜን!” ይበል።

16. “አባቱን ወይም እናቱን የሚያቃልል የተረገመ ይሁን።”ሕዝቡም ሁሉ፣ “አሜን! ይበል።

17. “የባልንጀራውን የድንበር ድንጋይ ከቦታው የሚያንቀሳቅስ የተረገመ ይሁን።”ሕዝቡም ሁሉ፣ “አሜን!” ይበል።

18. “ዐይነ ስውሩን በተሳሳተ መንገድ የሚመራ፣ የተረገመ ይሁን።”ሕዝቡም ሁሉ፣ “አሜን!” ይበል።

19. “በመጻተኛው፣ አባት በሌለውና በመበለቲቱ ላይ ፍትሕ የሚያዛባ የተረገመ ይሁን።”ሕዝቡም ሁሉ፣ “አሜን!” ይበል።

ዘዳግም 27