1. ሙሴና የእስራኤል አለቆች ሕዝቡን እንዲህ ብለው አዘዙ፤ “ዛሬ የማዛችሁን እነዚህን ትእዛዞች ሁሉ ጠብቁ፤
2. አምላክህ እግዚአብሔር (ኤሎሂም ያህዌ) ወደሚሰጥህ ምድር ለመግባት ዮርዳኖስን በተሻገራችሁ ጊዜ፣ ጥቂት ትልልቅ ድንጋዮችን አቁምና በኖራ ቅባቸው።
3. የአባቶችህ አምላክ እግዚአብሔር (ኤሎሂም ያህዌ) በሰጠህ ተስፋ መሠረት፣ ማርና ወተት ወደምታፈሰው አምላክህ እግዚአብሔር (ኤሎሂም ያህዌ) ወደሚሰጥህ ምድር ለመግባት ዮርዳኖስን ስትሻገር፣ የዚህን ሕግ ቃላት ሁሉ ጻፍባቸው።
4. ዮርዳኖስን እንደ ተሻገርህም፣ ዛሬ ባዘዝሁህ መሠረት እነዚህን ድንጋዮች በጌባል ተራራ ላይ ትከላቸው፤ በኖራም ቅባቸው።
5. እዚያም ለአምላክህ ለእግዚአብሔር (ኤሎሂም ያህዌ) የድንጋይ መሠዊያ ሥራ፤ በድንጋዮቹም ላይ ማናቸውንም የብረት መሣሪያ አታሳርፍባቸው።
6. የአምላክህን የእግዚአብሔርን (ኤሎሂም ያህዌ) መሠዊያ ካልተጠረበ ድንጋይ ሥራ፤ በላዩም ለአምላክህ ለእግዚአብሔር (ኤሎሂም ያህዌ) የሚቃጠል መሥዋዕት አቅርብበት።
7. በዚያም የኅብረት መሥዋዕት ሠዋ፤ ብላም፣ በአምላክህ በእግዚአብሔር (ኤሎሂም ያህዌ) ፊት ደስ ይበልህ።
8. በድንጋዮቹ ላይ የዚህን ሕግ ቃላት ሁሉ ግልጽ አድርገህ ጻፍባቸው።”
9. ሙሴና ሌዋውያን ካህናትም ለእስራኤል ሁሉ እንዲህ አሉ፤ “እስራኤል ሆይ፤ ጸጥ ብለህ አድምጥ! አንተ ዛሬ የአምላክህ የእግዚአብሔር (ኤሎሂም ያህዌ) ሕዝብ ሆነሃል፤
10. አምላክህን እግዚአብሔርን (ኤሎሂም ያህዌ) ታዘዝ፤ ዛሬ የምሰጥህን ትእዛዙንና ሥርዐቱን ጠብቅ።”
11. ሙሴ በዚያኑ ዕለት ሕዝቡን እንዲህ ብሎ አዘዘ፦
12. ዮርዳኖስን በተሻገራችሁ ጊዜ፣ ስምዖን፣ ሌዊ፣ ይሁዳ፣ ይሳኮር፣ ዮሴፍና ብንያም ሕዝቡን ለመባረክ በገሪዛን ተራራ ላይ ይቁሙ።
13. ሮቤል፣ ጋድ፣ አሴር፣ ዛብሎን፣ ዳንና ንፍታሌምም በጌባል ተራራ ላይ ለመርገም ይቁሙ።
14. ሌዋውያን ድምፃቸውን ከፍ አድርገው ለእስራኤል ሕዝብ ሁሉ እንዲህ ብለው ይናገሩ፦
15. “የእጅ ጥበብ ባለ ሙያ የሠራውን፣ በእግዘአብሔር (ያህዌ) ዘንድ አስጸያፊ የሆነውን ምስል የሚቀርጽ ወይም ጣዖትን የሚያበጅ፣ በስውርም የሚያቆም ሰው የተረገመ ይሁን።”ሕዝቡም ሁሉ፣ “አሜን!” ይበል።