ዘዳግም 24:9-19 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

9. ከግብፅ ከወጣችሁ በኋላ በመንገድ ላይ ሳላችሁ አምላክህ እግዚአብሔር (ኤሎሂም ያህዌ) በማርያም ላይ ያደረገባትን አስታውሱ።

10. ማናቸውንም ነገር ለባልንጀራህ ስታበድር መያዣ አድርጎ የሚሰጥህን ለመቀበል ወደ ቤቱ አትግባ።

11. አንተ ከውጭ ሆነህ ጠብቅ፤ ያበደርኸውም ሰው መያዣውን ከቤት ያምጣልህ።

12. ሰውየው ድኻ ከሆነ፣ መያዣውን ከአንተ ዘንድ አታሳድርበት።

13. መደረቢያውን ለብሶት እንዲያድር ፀሓይ ሳትጠልቅ መልስለት። ከዚያም ያመሰግንሃል፤ በአምላክህ በእግዚአብሔር (ኤሎሂም ያህዌ) ፊትም የጽድቅ ሥራ ሆኖ ይቈጠርልሃል።

14. ድኻና ችግረኛ የሆነውን የምንዳ ሠራተኛ እስራኤላዊ ወንድምህም ሆነ፣ ከከተሞችህ ባንዲቱ የሚኖረውን መጻተኛ አትበዝብዘው፤

15. የሠራበትን ሒሳብ በዕለቱ፣ ፀሓይ ሳትጠልቅ ክፈለው፤ ድኻ በመሆኑ በጒጒት ይጠባበቀዋልና። ያለበለዚያ ወደ እግዚአብሔር (ያህዌ) ይጮኽና ኀጢአት ይሆንብሃል።

16. አባቶች ስለ ልጆቻቸው፣ ልጆችም ስለ አባቶቻቸው አይገደሉ፤ እያንዳንዱ በራሱ ኀጢአት ይገደል።

17. ለመጻተኛው ወይም አባት ለሌለው ልጅ ፍትሕ አትንፈገው፤ የመበለቲቱንም መደረቢያ መያዣ አታድርግ።

18. አንተም በግብፅ ባሪያ እንደ ነበርህና አምላክህ እግዚአብሔር (ኤሎሂም ያህዌ) ከዚያ እንደ ተቤዠህ አስታውስ፤ ይህን እንድታደርግ ያዘዝሁህ ለዚህ ነው።

19. የዕርሻህን ሰብል በምታጭድበት ጊዜ፣ ተረስቶ የቀረ ነዶ ቢኖር፣ ያን ለመውሰድ ተመልሰህ አትሂድ። አምላክህእግዚአብሔር (ኤሎሂም ያህዌ) በእጅህ ሥራ ሁሉ እንዲባርክህ ነዶውን ለመጻተኛው፣ አባት ለሌለውና ለመበለቲቱ ተወው።

ዘዳግም 24