6. በሕይወት ዘመንህ ሁሉ ሰላምን ለእነርሱ አትመኝ።
7. ወንድምህ ስለ ሆነ ኤዶማዊውን አትጸየፈው፤ መጻተኛ ሆነህ በአገሩ ኖረሃልና ግብፃዊውን አትጥላው።
8. ለእነርሱ የተወለዱላቸው የሦስተኛው ትውልድ ልጆች ወደ እግዚአብሔር (ያህዌ) ጉባኤ መግባት ይችላሉ።
9. ጠላትህን ለመውጋት ወጥተህ በሰፈርህ ጊዜ፤ ከማናቸውም ርኵሰት ራስህን ጠብቅ።
10. ከመካከላችሁ ሌሊት ዘር በማፍሰስ የረከሰ ሰው ቢኖር ከሰፈር ወጥቶ እዚያው ይቈይ።
11. እየመሸ ሲመጣ ግን ገላውን ይታጠብ፤ ፀሓይ ስትጠልቅም ወደ ሰፈሩ ይመለስ።
12. ለመጸዳጃ የሚሆንህን ቦታ ከሰፈር ውጭ አዘጋጅ።
13. ከትጥቅህም ጋር መቈፈሪያ ያዝ፤ በምትጸዳዳበት ጊዜ ዐፈር ቈፍረህ በዐይነ ምድርህ ላይ መልስበት።
14. አምላክህ እግዚአብሔር (ኤሎሂም ያህዌ) ሊጠብቅህ ጠላቶችህንም በእጅህ አሳልፎ ሊሰጥህ በሰፈር ውስጥ ስለሚዘዋወር፣ በመካከልህ አንዳች ነውር አይቶ ከአንተ እንዳይመለስ፣ ሰፈርህ የተቀደሰ ይሁን።
15. አንድ ባሪያ ከአሳዳሪው ኰብልሎ ወደ አንተ ቢመጣ፣ ለአሳዳሪው አሳልፈህ አትስጠው።
16. ደስ በሚያሰኘው ቦታና ራሱ በመረጠው ከተማ በመካከልህ ይኑር፤ አንተም አታስጨንቀው።
17. ወንድ ወይም ሴት እስራኤላዊ የቤተ ጣዖት አመንዝራ አይሁን።