ዘዳግም 22:14-24 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

14. ስሟንም በማጥፋት፣ “ይህችን ሴት አገባኋት፤ ዳሩ ግን በደረስሁባት ጊዜ ድንግልናዋን አላገኘሁም” ቢል፣

15. የልጂቱ አባትና እናት ድንግልናዋን የሚያረጋግጥ ማስረጃ ይዘው በከተማዪቱ በር ወዳሉት አለቆች ይምጡ።

16. የልጂቱም አባት ለአለቆቹ እንዲህ ይበል፤ “ልጄን ለዚህ ሰው ዳርሁለት፤ እርሱ ግን ጠላት፤

17. ስሟንም በማጥፋት፣ ‘ልጅህን ከነድንግልናዋ አላገኘኋትም’ ብሎኛል፤ ነገር ግን የልጄ ድንግልና ማረጋገጫ ይኸውላችሁ፤” ከዚያም ወላጆቿ የደሙን ሸማ በከተማዪቱ አለቆች ፊት ይዘርጉት።

18. ከዚያም በኋላ አለቆቹ ሰውየውን ይዘው ይቅጡት፤

19. ይህ ሰው የአንዲት እስራኤላዊት ድንግል ስም አጥፍቶአልና አንድ መቶ ሰቅል ብር ያስከፍሉት፤ ገንዘቡንም ለልጂቱ አባት ይስጡት፤ ሴቲቱም ሚስቱ ሆና ትኖራለች፤ በሕይወት ዘመኑ ሁሉ ሊፈታት አይችልም።

20. ሆኖም ክሱ እውነት ሆኖ ሴቲቱ ድንግል ለመሆኗ ምንም ማረጋገጫ ማቅረብ ካልተቻለ፣

21. ገና በአባቷ ቤት ሳለች በማመንዘር በእስራኤል ውስጥ ወራዳ ተግባር ፈጽማለችና ወደ አባቷ ቤት ደጃፍ ያምጧት፤ እዚያም የከተማዋ ሰዎች እስክትሞት ድረስ በድንጋይ ይውገሯት። ክፉውን ከመካከልህ ማስወገድ አለብህ።

22. አንድ ሰው፣ ከሌላ ሰው ሚስት ጋር ተኝቶ ቢገኝ፣ አብሮአት የተኛው ሰውና ሴቲቱ ሁለቱም ይገደሉ፤ ክፉውን ከእስራኤል ማስወገድ አለብህ።

23. አንድ ሰው የታጨች ድንግል በከተማ ውስጥ አግኝቶ ከእርሷ ጋር ቢተኛ፣

24. ልጃገረዲቱ በከተማ ውስጥ እያለች አስጥሉኝ ብላ ስላልጮኸች፣ ሰውየውም የሌላን ሰው ሚስት አስገድዶ ስለደፈረ፣ ሁለቱንም ወደ ከተማ ደጃፍ ወስዳችሁ እስኪሞቱ ድረስ በድንጋይ ውገሯቸው። ክፉውን ከመካከልህ ማስወገድ አለብህ።

ዘዳግም 22