ዘዳግም 21:8-20 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

8. እግዚአብሔር (ያህዌ) ሆይ፤ ስለ ተቤዥኸው ሕዝብህ ስለ እስራኤል ብለህ ይህን ስርየት ተቀበል፤ ሕዝብህንም በፈሰሰው ንጹሕ ደም በደለኛ አታድርግ።” ስለ ፈሰሰውም ደም ስርየት ይደረግላቸዋል።

9. አንተም በእግዚአብሔር (ያህዌ) ፊት ቀና የሆነውን ስታደርግ፣ የንጹሑን ደም የማፍሰስ በደልን ከመካከልህ ታስወግዳለህ።

10. ከጠላቶችህ ጋር ጦርነት ልትገጥም ወጥተህ አምላክህ እግዚአብሔር (ኤሎሂም ያህዌ) እነርሱን በእጅህ አሳልፎ ሰጥቶህ በማረክህ ጊዜ፣

11. ከምርኮኞቹ መካከል መልከ መልካም ሴት አይተህ ብትማርክህ፣ ሚስትህ ልታደርጋት ትችላለህ።

12. ወደ ቤትህ ውሰዳት፤ ጠጒሯን ትላጭ፤ ጥፍሯንም ትቍረጥ።

13. ስትማረክ የለበሰችውንም ልብስ ታውልቅ፤ እቤትህ ተቀምጣ ለአባትና ለእናቷ ወር ሙሉ ካለቀሰችላቸው በኋላ፣ ልትደርስባትና ባል ልትሆናት፣ እርሷም ሚስት ልትሆንህ ትችላለች።

14. በእርሷ ደስተኛ ባትሆን፣ ወደምትፈልገው አንድትሄድ ነጻነት ስጣት፤ ውርደት ላይ ጥለሃታልና ልትሸጣት ወይም እንደ ባሪያ ልትቈጥራት አይገባህም።

15. አንድ ሰው ሁለት ሚስቶች ቢኖሩት፤ አንደኛዋን የሚወዳት፣ ሌላዋን ግን የሚጠላት ቢሆን፣ ሁለቱም ወንዶች ልጆችን ወልደውለት በኵር ልጁ ግን የተወለደው ከማይወዳት ሚስቱ ቢሆን፣

16. ንብረቱን ለልጆቹ በሚያወርስበት ጊዜ፣ የብኵርናን መብት ከማይወዳት ሚስቱ ከወለደው በኵር ልጅ ገፎ፣ ከሚወዳት ሚስቱ ለተወለደው ልጁ፣ በአድልዎ መስጠት አይገባውም፤

17. ይልቁንም ከተጠላችው ሚስቱ ለተወለደው ልጅ ካለው ሀብት ሁሉ ሁለት እጅ ድርሻውን በመስጠት ብኵርናውን ያስታውቅ፤ ያ ልጅ የአባቱ ኀይል መጀመሪያ ነውና፤ የብኵርና መብት የራሱ ነው።

18. አንድ ሰው፣ የአባቱን ወይም የእናቱን ትእዛዝ የማይሰማ፣ ቢቀጡትም የማይታረም እልከኛና ዐመፀኛ ልጅ ቢኖረው፣

19. አባትና እናቱ ይዘው በሚኖሩበት ከተማ በር ወዳሉት አለቆች ያምጡት፤

20. “ይህ ልጃችን እልከኛና ዐመፀኛ ነው፤ አይታዘዘንም፤ አባካኝና ሰካራም ነው” ብለው ለአለቆች ይንገሯቸው።

ዘዳግም 21