ዘዳግም 2:1-7 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

1. ከዚያም እግዚአብሔር (ያህዌ) ባዘዘኝ መሠረት ተመለስን፤ ቀይ ባሕርን ይዘን ወደ ምድረ በዳው ተጓዝን፤ በሴይር ኰረብታማ አገር ዙሪያ ለረጅም ጊዜ ተንከራተትን።

2. ከዚያም እግዚአብሔር (ያህዌ) እንዲህ አለኝ፤

3. “በዚህ በኰረብታማ አገር ዙሪያ እስኪበቃችሁ ተንከራታችኋል፤ አሁን ግን ወደ ሰሜን ተመለሱ።

4. ለሕዝቡም እነዚህን ትእዛዞች ስጣቸው፤ ሴይር በሚኖሩት በወንድሞቻችሁ በዔሳው ዘሮች ግዛት ዐልፋችሁ ትሄዳላችሁ፤ እነርሱ ይፈሯችኋል፤ ቢሆንም ከፍ ያለ ጥንቃቄ አድርጉ።

5. ከየትኛውም ምድራቸው ላይ ለጫማችሁ መርገጫ ታህል እንኳ መሬት ስለማልሰጣችሁ፣ ለጦርነት አታነሣሷቸው። ኰረብታማውን የሴይርን አገር ርስት አድርጌ ለዔሳው ሰጥቼዋለሁ።

6. ከዚያ ለምትበሉት ምግብም ሆነ ለምትጠጡት ውሃ በጥሬ ብር ትከፍሏቸዋላችሁ።”

7. አምላካችሁ እግዚአብሔር (ኤሎሂም ያህዌ) በእጃችሁ ሥራ ሁሉ ባርኮአችኋል፤ በዚህ ጭልጥ ባለው ምድረ በዳ ባደረጋችሁት ጒዞ ጠብቆአችኋል። በእነዚህ አርባ ዓመታት እግዚአብሔር ከእናንተ ጋር ነበርና አንዳችም ነገር አላጣችሁም።

ዘዳግም 2