1. ሌዋውያን ካህናት፣ የሌዊ ነገድም ሁሉ ከእስራኤል ጋር የመሬት ድርሻ ወይም ርስት አይኖራቸውም፤ ለእግዚአብሔር (ያህዌ) በእሳት ከሚቀርበው መባ ይብሉ፣ ድርሻቸው ነውና።
2. በወንድሞቻቸው መካከል ርስት አይኖራቸውም፤ በሰጣቸው ተስፋ መሠረት እግዚአብሔር (ያህዌ) ርስታቸው ነው።
3. ኰርማ ወይም በግ የሚሠዋው ሕዝብ ለካህኑ የሚሰጠው ድርሻ ወርቹን፣ መንገጭላውንና ሆድ ዕቃውን ነው።
4. የእህልህን፣ የአዲሱን ወይንህንና የዘይትህን በኵራት እንዲሁም ከበጎችህ በመጀመሪያ የተሸለተውን ጠጒር ትሰጣለህ፤
5. በእግዚአብሔር (ያህዌ) ስም ቆሞ ለዘላለም ያገለግል ዘንድ አምላክህ እግዚአብሔር (ኤሎሂም ያህዌ) ከነገዶችህ ሁሉ እርሱንና ዘሮቹን መርጦአል።