ዘዳግም 18:1-13 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

1. ሌዋውያን ካህናት፣ የሌዊ ነገድም ሁሉ ከእስራኤል ጋር የመሬት ድርሻ ወይም ርስት አይኖራቸውም፤ ለእግዚአብሔር (ያህዌ) በእሳት ከሚቀርበው መባ ይብሉ፣ ድርሻቸው ነውና።

2. በወንድሞቻቸው መካከል ርስት አይኖራቸውም፤ በሰጣቸው ተስፋ መሠረት እግዚአብሔር (ያህዌ) ርስታቸው ነው።

3. ኰርማ ወይም በግ የሚሠዋው ሕዝብ ለካህኑ የሚሰጠው ድርሻ ወርቹን፣ መንገጭላውንና ሆድ ዕቃውን ነው።

4. የእህልህን፣ የአዲሱን ወይንህንና የዘይትህን በኵራት እንዲሁም ከበጎችህ በመጀመሪያ የተሸለተውን ጠጒር ትሰጣለህ፤

5. በእግዚአብሔር (ያህዌ) ስም ቆሞ ለዘላለም ያገለግል ዘንድ አምላክህ እግዚአብሔር (ኤሎሂም ያህዌ) ከነገዶችህ ሁሉ እርሱንና ዘሮቹን መርጦአል።

6. አንድ ሌዋዊ ከሚኖርበት ከየትኛውም በእስራኤል ካሉት ከተሞችህ መካከል በፍጹም ፈቃድ እግዚአብሔር (ያህዌ) ወደሚመርጠው ስፍራ ቢመጣ፣

7. በእግዚአብሔር (ያህዌ) ፊት ቆመው እንደሚያገለግሉት ሌዋውያን ወንድሞቹ፣ እርሱም በአምላኩበእግዚአብሔር (ኤሎሂም ያህዌ) ስም ያገልግል።

8. ከቤተ ሰቡ ንብረት ሽያጭ ላይ ገንዘብ ቢቀበል እንኳ፣ ባልንጀሮቹ ከሚያገኙት ጥቅም እኩል ይካፈላል።

9. አምላክህ እግዚአብሔር (ኤሎሂም ያህዌ) ወደሚሰጥህ ምድር በምትገባበት ጊዜ፣ በዚያ የሚኖሩት አሕዛብ የሚፈጽሙትን አስጸያፊ መንገድ አትከተል።

10. በመካከልህ ወንድ ወይም ሴት ልጁን በእሳት የሚሠዋ ሟርተኛ፣ ወይም መተተኛ፣ ሞራ ገለጭ፣ ጠንቋይ

11. ወይም በድግምት የሚጠነቍል፤ መናፍስት ጠሪ ወይም ሙት አነጋጋሪ በመካከልህ ከቶ አይገኝ።

12. እነዚህን የሚያደርግ ሁሉ በእግዚአብሔር (ያህዌ) ዘንድ አስጸያፊ ነውና፣ ከእነዚህ አጸያፊ ልምዶች የተነሣም አምላክህእግዚአብሔር (ኤሎሂም ያህዌ) እነዚያን አሕዛብ ከፊትህ ያባርራቸዋል።

13. በአምላክህ በእግዚአብሔር (ኤሎሂም ያህዌ) ፊት ነውር አልባ ሁን።

ዘዳግም 18