6. ሰኰናው ስንጥቅ የሆነውን፣ ለሁለት የተከፈለውንና የሚያመሰኳ ማናቸውንም እንስሳ ብላ።
7. ነገር ግን ከሚያመሰኩት ወይም ሰኰናቸው ከተሰነጠቀ እንስሳት መካከል ግመልን፣ ጥንቸልንና ሽኮኮን አትብሉ፤ እነርሱ ቢያመሰኩ እንኳ፣ ሰኰናቸው የተሰነጠቀ ባለመሆኑ፣ በሥርዐቱ መሠረት በእናንተ ዘንድ ርኩሶች ናቸው።
8. ዐሳማም እንደዚሁ ርኩስ ነው፤ ምንም እንኳ ሰኰናው የተሰነጠቀ ቢሆንም፣ ስለማያመሰኳ፣ እርሱ ለእናንተ ንጹሕ አይደለም፤ የእነዚህን ሥጋ አትብሉ፤ ጥምባቸውንም አትንኩ።
9. በውሃ ውስጥ ከሚኖሩ ፍጡራን ሁሉ ክንፍና ግልፋፊ ያለውን ማናቸውንም ብሉ፤
10. ክንፍና ግልፋፊ የሌለውን ግን አትብሉ፤ ለእናንተ ርኩስ ነው።
11. ንጹሕ የሆነውን ወፍ ሁሉ መብላት ትችላላችሁ።
12. የሚከተሉትን ግን አትበሉም፤ እነርሱም፦ ንስር፣ ገዴ፣ ዓሣ አውጪ፣
13. ጭልፊት፣ ጭላት፣ ማናቸውም ዐይነት አድኖ በል አሞራ፣
14. ማናቸውም ዐይነት ቁራ፣
15. ሰጎን፣ ጠላቋ፣ ዝዪ፣ ማናቸውም ዐይነት በቋል፣
16. ጒጒት፣ ጋጋኖ፣ የውሃ ዶሮ፣
17. ይብራ፣ ጥንብ አንሣ አሞራ፣ እርኩም፣
18. ሽመላ፣ ማናቸውም ዐይነት ሳቢሳ፣ ጅንጅላቴ ወፍና የሌሊት ወፍ ናቸው።
19. ክንፍ ያላቸው ጥቃቅን ነፍሳት ሁሉ ለእናንተ ርኩስ ናቸው፤ እነርሱን አትብሏቸው።
20. ንጹሕ የሆነውን ማናቸውንም ክንፍ ያለውን ፍጡር ግን ብሉ።
21. አንተ ግን ለአምላክህ ለእግዚአብሔር (ኤሎሂም ያህዌ) ቅዱስ ሕዝብ ነህና የሞተውን ሁሉ አትብላ፤ ከከተሞችህ በአንዲቱ ለሚኖር መጻተኛ ስጠው፤ ይብላውም፤ ለውጭ አገር ሰው ሽጠው። የፍየልን ግልገል በእናቱ ወተት አትቀቅል።