8. እስራኤላውያን ከወረሷት ምድር ላይ ለሌዋውያኑ የምትሰጧቸው ከተሞች እያንዳንዱ ነገድ እንዳለው ድርሻ መጠን ይሆናል። ብዙ ካለው ነገድ ላይ ብዙ ከተሞች እንዲሁም ጥቂት ካለው ነገድ ላይ ጥቂት ከተሞችን ውሰዱ።”
9. ከዚያም እግዚአብሔር (ያህዌ) ሙሴን እንዲህ አለው፤
10. “እስራኤላውያንን እንዲህ ብለህ ንገራቸው፤ ‘ወደ ከነዓን ለመግባት ዮርዳኖስን በምትሻገሩበት ጊዜ፣
11. ሳያስበው ሰው የገደለ ሰው ሸሽቶ የሚጠጋባቸው ከተሞች እንዲሆኑ መማጸኛ ከተሞችን ምረጡ።
12. እነዚህም፣ ነፍሰ ገዳዩ በማኅበሩ ዘንድ ለፍርድ ከመቅረቡ በፊት እንዳይሞት ከደም ተበቃዩ የሚሸሽባቸው የመማጸኛ ከተሞች ይሆናሉ።
13. እነዚህ ለሌዋውያኑ የምትሰጧቸው ስድስት ከተሞች መማጸኛ ከተሞቻችሁ ይሆናሉ።
14. ስለዚህ ከዮርዳኖስ ወዲህ ሦስቱን እንዲሁም በከነዓን ሦስቱን የመማጸኛ ከተሞች አድርጋችሁ ስጡ።
15. እነዚህም ስድስት ከተሞች ሳያስበው ሰው የገደለ ማንኛውም ሰው እንዲሸሽባቸው ለእስራኤላውያን፣ ለመጻተኞችና በመካከላቸው ለሚኖር ለማንኛውም ሕዝብ የመማጸኛ ቦታዎች ይሆናሉ።
16. “ ‘አንድ ሰው ሌላውን እንዲሞት በብረት ቢመታው ነፍሰ ገዳይ ነው፤ በሞትም ይቀጣል።
17. ወይም አንድ ሰው መግደል የሚችል ድንጋይ በእጁ ቢይዝና ሌላውን ሰው እንዲሞት ቢመታው ነፍሰ ገዳይ ነው፤ በሞትም ይቀጣል።
18. ወይም አንድ ሰው መግደል የሚችል ዕንጨት በእጁ ቢይዝና ሌላውን ሰው እንዲሞት ቢመታው ነፍሰ ገዳይ ነው፤ በሞትም ይቀጣል።