ዘኁልቍ 32:3-22 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

3. “አጣሮት፣ ዲቦን፣ ኢያዜር፣ ኒምራ፣ ሐሴቦን፣ ኤልያሊ፣ ሴባማ፣ ናባውና፣ ባያን፣

4. እግዚአብሔር (ያህዌ) በእስራኤል ሕዝብ ፊት እንዲሸነፍ ያደረገው ይህ ሁሉ ምድር ለከብት ምቹ ነው፤ እኛ አገልጋዮችህም ከብቶች አሉን።

5. በፊትህ ሞገስ ያገኘን ከሆነ ይህ ምድር ለእኛ ለአገልጋዮችህ በርስትነት ይሰጠን፤ ዮርዳኖስንም እንድንሻገር አታድርገን።”

6. ሙሴም የጋድንና የሮቤልን ነገዶች እንዲህ አላቸው፤ “እናንተ እዚህ ተቀምጣችሁ ወገኖቻችሁ ወደ ጦርነት ይሂዱ?

7. እስራኤላውያን ተሻግረው እግዚአብሔር (ያህዌ) ወደ ሰጣቸው ምድር እንዳይገቡ ተስፋ የምታስቈርጧቸው ለምድን ነው?

8. አባቶቻችሁ ምድሪቱን እንዲሰልሉ ከቃዴስ በርኔ በላክኋቸው ጊዜም ያደረጉት ይህንኑ ነበር።

9. ወደ ኤሽኮል ሸለቆ ሄደው ምድሪቱን ካዩ በኋላ፣ እግዚአብሔር (ያህዌ) ወደ ሰጣቸው ምድር እንዳይገቡ እስራኤላውያንን ተስፋ አስቈረጧቸው።

10. በዚያም ቀን የእግዚአብሔር (ያህዌ) ቊጣ ነደደ፤ እንዲህም ሲል ማለ፤

11. ‘በፍጹም ልባቸው ስላልተከተሉኝ ከግብፅ ከወጡት፣ ዕድሜያቸው ሃያ ዓመትና ከዚያ በላይ የሆናቸው ሰዎች አንዳቸውም ለአብርሃም፣ ለይስሐቅና ለያዕቆብ ልሰጥ በመሐላ ቃል የገባሁላቸውን ምድር አያዩዋትም፤

12. እግዚአብሔርን (ያህዌ) በፍጹም ልባቸው ተከትለውታልና፣ ከቄኔዛዊው ከዮፎኒ ልጅ ከካሌብና ከነዌ ልጅ ከኢያሱ በስተቀር አንዳቸውም አያዩዋትም።’

13. የእግዚአብሔርም (ያህዌ) ቊጣ በእስራኤል ላይ ስለ ነደደ፣ በፊቱ ክፉ ነገር ያደረገው ያ ትውልድ በሙሉ እስኪያልቅ ድረስ አርባ ዓመት በምድረ በዳ እንዲንከራተቱ አደረጋቸው።

14. “እናንት የኀጢአተኞች ልጆች ይኸው በአባቶቻችሁ እግር ተተክታችሁ እግዚአብሔር (ያህዌ) በእስራኤል ላይ ይበልጥ እንዲቈጣ ታደርጋላችሁ።

15. እርሱን ከመከተል ብትመለሱ አሁንም ይህን ሁሉ ሕዝብ በምድረ በዳ ይተወዋል፤ ለሚደርስበትም ጥፋት ምክንያቱ እናንተው ትሆናላችሁ።”

16. ከዚህ በኋላ ወደ እርሱ ቀርበው እንዲህ አሉት፤ “እዚህ ለከብቶቻችን በረቶች፣ ለሴቶቻችንና ለልጆቻችን ከተሞች መሥራት እንወዳለን፤

17. ይሁን እንጂ ወደ ስፍራቸው እስክናገባቸው ድረስ ታጥቀንና በእስራኤላውያን ፊት ግንባር ቀደም ሆነን ለመሄድ ዝግጁ ነን፤ በዚህም ጊዜ ሴቶቻችንና ልጆቻችን በምድሪቱ ላይ ካሉት ነዋሪዎች እንዲጠበቁ በተመሸጉ ከተሞች ይኖራሉ።

18. እኛም እያንዳንዱ እስራኤላዊ ርስቱን እስኪወርስ ድረስ ወደየቤታችን አንመለስም።

19. ድርሻችንን ከዮርዳኖስ ወንዝ በስተ ምሥራቅ ስላገኘን፣ ከዮርዳኖስ ማዶ ከእነርሱ ጋር የምንካፈለው አንዳችም ርስት አይኖርም።”

20. ከዚያም ሙሴ እንዲህ አላቸው፤ “ይህን ብታደርጉ ማለትም በእግዚአብሔር (ያህዌ) ፊት ታጥቃችሁ ለጦርነት ብትዘጋጁ፣

21. እንዲሁም ጠላቶቹን ከፊቱ አሳዶ እስኪያስወጣ ድረስ ሁላችሁም በእግዚአብሔር ፊት ለጦርነት ዝግጁ ሆናችሁ ዮርዳኖስን ብትሻገሩ፣

22. ምድሪቱ ለእግዚአብሔር (ያህዌ) ከተገዛች በኋላ ልትመለሱ ትችላላችሁ፤ ለእግዚአብሔርና (ያህዌ) ለእስራኤል ካለባችሁም ግዴታ ነጻ ትሆናላችሁ፤ ይህችም ምድር በእግዚአብሔር (ያህዌ) ፊት ርስታችሁ ትሆናለች።

ዘኁልቍ 32