ዘኁልቍ 31:6-26 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

6. ሙሴም የቤተ መቅደሱን ንዋየ ቅዱሳትና ምልክት መስጫ የሆኑትን መለከቶች ከያዘው ከካህኑ ከአልዓዛር ልጅ ከፊንሐስ ጋር ከየነገዱ አንዳንድ ሺህ ሰው ለጦርነት ላከ።

7. እግዚአብሔር (ያህዌ) ሙሴን ባዘዘው መሠረት ከምድያም ጋር ተዋጉ፤ ወንዱንም በሙሉ ፈጁት፤

8. ከተገደሉትም መካከል አምስቱ የምድያም ነገሥታት ኤዊ፣ ሮቆም፣ ሱር፣ ሑርና ሪባ ይገኙባቸዋል፤ የቢዖርን ልጅ በለዓምንም በሰይፍ ገደሉት።

9. ከዚያም እስራኤላውያን የምድያማውያን ሴቶችና ሕፃናት ማረኩ፤ የቀንድ ከብቶቻቸውን፣ የበግና የፍየል መንጋዎቻቸውን ሁሉ ነዱ፤ ሀብታቸውንም በሙሉ ወሰዱ።

10. ምድያማውያኑ የሚኖሩባቸውን ከተሞች ሁሉ ሰፈሮቻቸውንም በሙሉ አቃጠሉ።

11. ሰውና እንስሳትን ጨምሮ የማረኩትንና የዘረፉትን ሁሉ እንዳለ አጋዙት።

12. የማረኳቸውን ሰዎች፣ የነዱአቸውን እንስሳትና የዘረፉትን ሀብት በሙሉ፣ ከኢያሪኮ ማዶ፣ በዮርዳኖስ አጠገብ፣ በሞዓብ ወዳለው፣ ሙሴና ካህኑ አልዓዛር እንዲሁም መላው የእስራኤላውያን ማኅበር ወዳሉበት ሰፈራቸው አመጡአቸው።

13. ሙሴ፣ ካህኑ አልዓዛርና የማኅበረ ሰቡ መሪዎች በሙሉ ሊቀበሉአቸው ከሰፈር ወጡ።

14. ሙሴም ከጦርነት በተመለሱት በሰራዊቱ አዛዦች ማለትም በሻለቆችና በመቶ አለቆች ላይ ተቈጣ።

15. እርሱም እንዲህ አላቸው፤ “ሴቶችን ሁሉ እንዴት በሕይወት ትተውአቸዋላችሁ?”

16. የበለዓምን ምክር ተቀብለው በፌጎር በተፈጸመው ድርጊት እስራኤላውያን ከእግዚአብሔር (ያህዌ) እንዲመለሱና የእግዚአብሔርም (ያህዌ) ሕዝብ እንዲቀሠፍ ያደረጉት እነርሱ ናቸው።

17. አሁንም ወንዶቹን ልጆች ሁሉ፣ ወንድ ያወቊትንም ሴቶች በሙሉ ግደሉዋቸው፤

18. ነገር ግን ወንድ ያላወቁትን ልጃገረዶች ሁሉ ለራሳችሁ አስቀሩአቸው።

19. “ከእናንት መካከል ሰው የገደለ ወይም የተገደለውን የነካ ሁሉ ከሰፈር ውጭ ሰባት ቀን ይቈይ። በሦስተኛውና በሰባተኛው ቀን ራሳችሁንና ምርኮኞቻችሁን አንጹ።

20. ማናቸውንም ልብስ እንዲሁም ከቈዳ፣ ከፍየል ጠጒር ወይም ከዕንጨት የተሠራ ማንኛውንም ነገር አንጹ።”

21. ከዚያም ካህኑ አልዓዛር ወደ ጦርነት ሄደው የነበሩትን ወታደሮች እንዲህ አላቸው፤ “እግዚአብሔር (ያህዌ) ለሙሴ የሰጠው የሕጉ ሥርዐት ይህ ነው፤

22. ወርቅ፣ ብር፣ ናስ፣ ብረት፣ ቈርቈሮ፣ እርሳስ

23. እንዲሁም እሳትን መቋቋም የሚችል ማንኛውም ነገር በእሳት ውስጥ ማለፍ አለበት፤ ከዚያም ንጹሕ ይሆናል፤ ይህም ሆኖ መንጻት አለበት። እሳትን መቋቋም የማይችል ማንኛውም ነገር በዚሁ ውሃ ውስጥ ማለፍ አለበት።

24. በሰባተኛው ቀን ልብሳችሁን እጠቡ፤ ትነጻላችሁም፤ ከዚያም ወደ ሰፈር መግባት ትችላላችሁ።”

25. እግዚአብሔር (ያህዌ) ሙሴን እንዲህ አለው፤

26. “አንተ፣ ካህኑ አልዓዛርና በማኅበረ ሰቡ ውስጥ ያሉት የየቤተ ሰቡ አለቆች ሆናችሁ የተማረከውን ሕዝብና እንስሳት ሁሉ ቊጠሩ።

ዘኁልቍ 31