ዘኁልቍ 23:1-8 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

1. በለዓም፣ “እዚህ ሰባት መሠዊያ ሥራልኝ፤ ሰባት ኮርማዎችና ሰባት አውራ በጎችም አዘጋጅልኝ” አለው።

2. ባላቅም በለዓም እንደ ነገረው አደረገ፤ ሁለቱም በእያንዳንዱ መሠዊያ ላይ አንድ ኮርማና አንድ አውራ በግ አቀረቡ።

3. ከዚያም በለዓም ባላቅን፣ “እኔ ወደዚያ ስሄድ፣ አንተ እዚሁ መሥዋዕትህ አጠገብ ቈይ፤ ምናልባትም እግዚአብሔር (ያህዌ) ሊገናኘኝ ይመጣ ይሆናል፤ የሚገልጥልኝንም ሁሉ እነግርሃለሁ” አለው። ከዚያም በለዓም ወደ አንድ ገላጣ ኰረብታ ሄደ።

4. እግዚአብሔር (ኤሎሂም) ተገናኘው፤ በለዓምም፣ “እነሆ፤ ሰባት መሠዊያዎች አዘጋጅቻለሁ፤ በእያንዳንዱም ላይ አንድ ኮርማና አንድ አውራ በግ አቅርቤአለሁ” አለው።

5. እግዚአብሔርም (ያህዌ) በበለዓም አፍ መልእክት አስቀምጦ፣ “ወደ ባላቅ ተመልሰህ ይህን መልእክት ንገረው” አለው።

6. እርሱም ተመልሶ ሲሄድ ባላቅን ከመላው የሞዓብ አለቆች ጋር በመሠዊያው አጠገብ ቆሞ አገኘው።

7. ከዚያም በለዓም ንግሩን እንዲህ ሲል ጀመረ፤“ባላቅ ከአራም አመጣኝ፣የሞዓብ ንጉሥ ከምሥራቅ ተራሮች።‘ና ያዕቆብን ርገምልኝ፤መጥተህም እስራኤልን አውግዝልኝ’ አለኝ።

8. እግዚአብሔር (ኤሎሂም) ያልረገመውን፣እኔ እንዴት ረግማለሁ? እግዚአብሔር (ያህዌ) ያላወገዘውንስ፣እንዴት አወግዛለሁ?

ዘኁልቍ 23