ዘኁልቍ 22:9-18 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

9. እግዚአብሔርም (ኤሎሂም) ወደ በለዓም መጥቶ፣ “ከአንተ ጋር ያሉት እነዚህ ሰዎች እነማን ናቸው?” ሲል ጠየቀው።

10. በለዓምም እግዚአብሔርን (ኤሎሂም) እንዲህ አለው፤ “የሞዓብ ንጉሥ የሴፎር ልጅ ባላቅ ይህን መልእክት ልኮብኛል፤

11. ‘ከግብፅ የወጣ ሕዝብ የምድሩን ገጽ አጥለቅልቆታል፤ ስለዚህ መጥተህ ርገምልኝ፤ ምናልባት ልዋጋቸውና ላባርራቸው የምችለው ከዚያ በኋላ ሊሆን ይችላል።’ ”

12. እግዚአብሔር (ኤሎሂም) ግን በለዓምን፣ “አብረሃቸው አትሂድ፤ የተባረከ ሕዝብ ስለ ሆነም አትርገመው” አለው።

13. በማግሥቱ ጠዋት በለዓም ተነሥቶ የባላቅን አለቆች፣ “አብሬአችሁ እንዳልሄድ እግዚአብሔር (ያህዌ) ከልክሎኛልና እናንተ ወደ አገራችሁ ተመለሱ አላቸው።”

14. ስለዚህ የሞዓብ አለቆች ወደ ባላቅ ተመልሰው፣ “በለዓም አብሮን ለመምጣት እምቢ አለን” አሉት።

15. ከዚያም ባላቅ ከፊተኞቹ ይልቅ ቍጥራቸው የበዛና ይበልጥ የተከበሩ ሌሎች አለቆች ላከ።

16. እነርሱም ወደ በለዓም መጥተው እንዲህ አሉት፤ “የሴፎር ልጅ ባላቅ ይህን እንድንነግርህ ልኮናል፤ ወደ እኔ ለመምጣት የሚያግድህ ምንም ነገር አይኑር፤

17. ወሮታህን በእጅጉ እከፍላለሁ፤ የምትለውንም ሁሉ አደርጋለሁ፤ ስለዚህ መጥተህ ይህን ሕዝብ ርገምልኝ።”

18. በለዓም ግን እንዲህ ሲል መለሰላቸው፤ “ሌላው ይቅርና ባላቅ በብርና በወርቅ የተሞላ ቤተ መንግሥቱን ቢሰጠኝ እንኳ፣ የአምላኬን የእግዚአብሔርን (ኤሎሂም ያህዌ) ትእዛዝ በመጣስ ከዚያ ያለፈ ወይም ያነሰ ማንኛውንም ነገር ማድረግ አልችልም።

ዘኁልቍ 22