1. በኔጌብ ይኖር የነበረው ከነዓናዊው የዓራድ ንጉሥ እስራኤል በአታሪም መንገድ መምጣቱን በሰማ ጊዜ በእስራኤላውያን ላይ አደጋ ጥሎ ጥቂቶቹን ማረከ።
2. በዚያን ጊዜ እስራኤል፣ “ይህን ሕዝብ አሳልፈህ በእጃችን ከሰጠኸን ከተሞቻቸውን ፈጽሞ እንደመስሳለን” ሲል ለእግዚአብሔር (ያህዌ) ተሳለ።
3. እግዚአብሔርም (ያህዌ) የእስራኤልን ልመና ሰምቶ ከነዓናውያንን በእጃቸው አሳልፎ ሰጣቸው፤ እነርሱም ሰዎቹንና ከተሞቻቸውን ፈጽመው ደመሰሱ፤ ከዚህ የተነሣም ስፍራው ሖርማ ተባለ።
4. እስራኤላውያን በኤዶም ዞረው ለመሄድ ስላሰቡ ከሖር ተራራ ተነሥተው ወደ ቀይ ባሕር በሚወስደው መንገድ ተጓዙ፤ ይሁን እንጂ ሕዝቡ በመንገድ ሳለ ትዕግሥቱ አለቀ፤
5. በእግዚአብሔርና (ኤሎሂም) በሙሴም ላይ ተነሥተው፣ “በምድረ በዳ እንድንሞት ከግብፅ ያወጣችሁን ለምንድ ነው? ምግብ የለ! ውሃ የለ! ይህን የማይረባ ምግብ ሰውነታችን ተጸይፎታል” ሲሉ ተናገሩ።
6. በዚህ ጊዜ እግዚአብሔር (ያህዌ) መርዘኛ እባቦች ሰደደባቸው፤ ሕዝቡን ነደፉ፤ ብዙ እስራኤላውያንም ሞቱ።
7. ሕዝቡም ወደ ሙሴ መጥቶ፣ “በእግዚአብሔርና (ያህዌ) በአንተ ላይ በመናገራችን በድለናል፤ እባቦቹን ከእኛ እንዲያርቅልን ወደ እግዚአብሔር (ያህዌ) ጸልይልን” አለ፤ ሙሴም ስለ ሕዝቡ ጸለየ።
8. እግዚአብሔር (ያህዌ) ሙሴን፣ “እባብ ሠርተህ በዕንጨት ላይ ስቀለው፤ የተነደፈውም ሁሉ ወደ እርሱ በማየት ይድናል” አለው፤
9. ስለዚህ ሙሴ የናስ እባብ ሠርቶ በዕንጨት ላይ ሰቀለ፤ ከዚያም በእባብ የተነደፈ ማናቸውም ሰው ወደ ናሱ እባብ በተመለከተ ጊዜ ይድን ነበር።