1. እግዚአብሔር (ያህዌ) ሙሴን እንዲህ አለው፤
2. “ለእስራኤላውያን ንገራቸውና ከየነገዱ አለቆች አንዳንድ፣ ባጠቃላይ ዐሥራ ሁለት በትር ተቀበል፤ የያንዳንዱንም ሰው ስም በየበትሩ ላይ ጻፈው።
3. ለያንዳንዱ የነገድ አለቃ አንዳንድ በትር መኖር ስላለበት በሌዊ በትር ላይ የአሮንን ስም ጻፍ።
4. በትሮቹንም እኔ ከአንተ ጋር በምገናኝበት በመገናኛው ድንኳን ውስጥ ከምስክሩ ፊት ለፊት አስቀምጣቸው።
5. እኔ የምመርጠው ሰው በትርም ታቈጠቍጣለች፤ እስራኤላውያን በእናንተ ላይ ነጋ ጠባ የሚያደርጉትንም ማጒረምረም በዚህ እገታለሁ።
6. ሙሴም ለእስራኤላውያን ተናገራቸው፤ አለቆቻቸውም በቀደሙት በያንዳንዱ አባቶች ስም ዐሥራ ሁለት በትር ሰጡት፤ የአሮን በትርም በበትሮቹ መካከል ነበረች።