ዘኁልቍ 16:30-38 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

30. ይሁን እንጂ እግዚአብሔር (ያህዌ) ፈጽሞ አዲስ የሆነ ነገር አምጥቶ ምድር አፏን ከፍታ እነርሱንና የእነርሱ የሆነውን ሁሉ ብትውጥና በሕይወታቸው ወደ መቃብር ቢወርዱ፣ ሰዎቹ እግዚአብሔርን (ያህዌ) የናቁ መሆናቸውን የምታውቁት ያን ጊዜ ነው።”

31. ይህን ሁሉ ተናግሮ እንደ ጨረሰ የቆሙባት ምድር ተሰነጠቀች፤

32. አፏንም ከፍታ ሰዎቹን ከነቤተ ሰቦቻቸው እንዲሁም የቆሬን ሰዎች በሙሉ፣ ንብረታቸውንም ሁሉ ዋጠች።

33. እነርሱም ካላቸው ከማናቸውም ነገር ጋር ከነሕይወታቸው ወደ መቃብር ወረዱ፤ ምድሪቱም በላያቸው ተከደነችባቸው፤ ጠፉ፤ ከማኅበረ ሰቡም ተወገዱ።

34. ከጩኸታቸውም የተነሣ በአካባቢያቸው የነበሩት እስራኤላውያን ሁሉ፣ “ምድሪቱ እኛንም እኮ ልትውጠን ነው” ብለው ሸሹ።

35. እሳትም ከእግዚአብሔር (ያህዌ) ዘንድ ወርዳ የሚያጥኑትን ሁለት መቶ አምሳ ሰዎች በላቻቸው።

36. እግዚአብሔርም (ያህዌ) ሙሴን እንዲህ አለው፤

37. “ጥናዎቹ የተቀደሱ ናቸውና ከተቃጠሉት ሰዎች ዘንድ ወስደህ በውስጣቸው ያለውን ፍም አርቆ እንዲደፋ ለካህኑ ለአሮን ልጅ ለአልዓዛር ንገረው፤

38. እነዚህም ሕይወታቸውን ለማጥፋት ኀጢአት የሠሩ ሰዎች ጥና ናቸው፤ ጥናዎቹም በእግዚአብሔር (ያህዌ) ፊት የቀረቡና የተቀደሱ በመሆናቸው ለመሠዊያው መለበጫ እንዲሆኑ ቀጥቅጠህ አሣሣቸው፤ እነዚህም ለእስራኤላውያን ማስጠንቀቂያ ይሁኑ።”

ዘኁልቍ 16