17. እያንዳንዱም ሰው ጥናውን ይወስዳል፤ ባጠቃላይ ሁለት መቶ አምሳ ጥናዎች ይሆናሉ፤ በዚያም ላይ ዕጣን ጨምሮ በእግዚአብሔር (ያህዌ) ፊት ያቀርባል፤ አንተና አሮንም ጥናዎቻችሁን እንደዚሁ ታቀርባላችሁ።
18. እያንዳንዱ ሰው ጥናውን በመያዝ ፍም አድርጎበት፣ ዕጣን ጨምሮበት ከሙሴና ከአሮን ጋር በመገናኛው ድንኳን ደጃፍ ቆመ።
19. ቆሬም እነርሱን በመቃወም ተከታዮቹን ሁሉ በመገናኛው ድንኳን ደጃፍ በሰበሰባቸው ጊዜ፣ የእግዚአብሔር (ያህዌ) ክብር ለመላው ማኅበር ተገለጠ።
20. እግዚአብሔርም (ያህዌ) ሙሴንና አሮንን እንዲህ አላቸው፤
21. “ሁሉንም በአንድ ጊዜ እንዳጠፋቸው እናንተ ከዚህ ማኅበር ተለዩ።”
22. ሙሴና አሮን ግን በግንባራቸው ተደፍተው፣ “የሰብአዊ ፍጡር ሁሉ መንፈስ አምላክ (ኤሎሂም) የሆንህ እግዚአብሔር (ያህዌ) ሆይ፤ አንድ ሰው ኀጢአት በሠራ በመላው ማኅበር ላይ ትቈጣለህን?” ሲሉ ጮኹ።
23. ከዚያም እግዚአብሔር (ያህዌ) ሙሴን እንዲህ አለው፤
24. “ማኅበሩን ‘ከቆሬ፣ ከዳታንና ከአቤሮን ድንኳኖች ራቁ’ በላቸው።”
25. ሙሴ ተነሥቶ ወደ ዳታንና አቤሮን ሄደ፤ የእስራኤልም ሽማግሌዎች ተከተሉት።
26. እርሱም፣ “ከእነዚህ ክፉ ሰዎች ድንኳን ራቍ የእነርሱ የሆነውን ማንኛውንም ነገር አትንኩ፤ ያለበለዚያ በእነርሱ ኀጢአት ሁሉ እናንተም ትጠፋላችሁ” ሲል ማኅበሩን አስጠነቀቀ።
27. ስለዚህ እነርሱ ከቆሬ፣ ከዳታንና ከአቤሮን ድንኳን ራቁ። ዳታንና አቤሮን ወጥተው ከሚስቶቻቸው፣ ከልጆቻቸውና ከሕፃናቶቻቸው ጋር በየድንኳኖቻቸው ደጃፍ ላይ ቆመው ነበር።