6. አሁን ግን የምግብ ፍላጎታችን ጠፍቶአል፤ ከዚህ መና በስተቀር የምናየው የለም!”
7. መናው እንደ ድንብላል ዘር ትንንሽ ሆኖ የሙጫ መልክ ነበረው።
8. ሕዝቡ ተዘዋውሮ በመልቀም በወፍጮ ከፈጨ ወይም በሙቀጫ ከወቀጠ በኋላ በምንቸት ይቀቅለው ወይም ይጋግረው ነበር፤ ጣዕሙም በወይራ ዘይት የተጋገረ ያህል ይጣፍጥ ነበር።
9. ጤዛው ሌሊት በሰፈር ላይ በሚወርድበት ጊዜ መናውም እንዲሁ ይወርድ ነበር።
10. ሙሴ፣ ሕዝቡ ሁሉ በየቤተ ሰቡ፣ በየድንኳኑ ደጃፍ ሆኖ ሲያለቅስ ሰማ። እግዚአብሔርም (ያህዌ) እጅግ ተቈጣ፤ ሙሴም ተጨነቀ።
11. እርሱም እግዚአብሔርን (ያህዌ) እንዲህ ሲል ጠየቀው፤ “እንዲህ ያለውን መከራ በባሪያህ ላይ ለምን አመጣህ? የዚህን ሕዝብ ሁሉ ሸክም የጫንህብኝስ ምን አስቀይሜህ ነው?
12. ይህን ሁሉ ሕዝብ የፀነስሁት እኔ ነኝን? እኔስ ወለድሁትን? ታዲያ ሞግዚት ሕፃን እንደምትታቀፍ በክንዴ ታቅፌ ለቀድሞ አባቶቻቸው ትሰጣቸው ዘንድ በመሐላ ቃል ወደ ገባህላቸው ምድር እንዳስገባቸው የምትነግረኝ ለምንድ ነው?
13. ለዚህ ሁሉ ሕዝብስ ሥጋ ከወዴት አመጣለሁ? ሁሉም ‘የምንበላው ሥጋ ስጠን’ እያሉ ያለቅሱብኛል።
14. እጅግ ከብዶኛልና ይህን ሁሉ ሕዝብ ብቻዬን ልሸከም አልችልም።
15. እንዲህስ ከምታደርገኝ በፊትህ ሞገስ አግኝቼ እንደሆነ አሁኑኑ ግደለኝ፤ የሚደርስብኝን ጥፋት አልይ።”
16. እግዚአብሔር (ያህዌ) ሙሴን እንዲህ አለው፤ “በሕዝቡ መካከል በመሪነትና በእልቅና ብቃት አላቸው የምትላቸውን ሰባ የእስራኤል ሽማግሌዎች አምጣልኝ፤ ካንተም ጋር ይቆሙ ዘንድ ወደ መገናኛው ድንኳን እንዲመጡ አድርግ።
17. ወደዚያም ወርጄ አነጋግርሃለሁ፤ ባንተ ላይ ካለው መንፈስ ወስጄ በእነርሱ ላይ አደርጋለሁ፤ የሕዝቡንም ሸክም ብቻህን እንዳትሸከም እነርሱ ያግዙሃል።