1. እግዚአብሔር (ያህዌ) ሙሴን እንዲህ አለው፤
2. “ማንኛውም ሰው በዐደራ የተሰጠውን ወይም በመያዣነት የተቀበለውን በመካድና ባልንጀራውን በማጭበርበር ኀጢአት ቢሠራ፣ እግዚአብሔርንም (ያህዌ) ቢበድል ወይም ባልንጀራውን ቢቀማው ወይም ቢያታልለው፣
3. ወይም የጠፋ ነገር አግኝቶ አላየሁም ቢል ወይም በሐሰት ቢምል ወይም ሰዎች የሚያደርጉትን እንዲህ ያለውን ማናቸውንም ኀጢአት ቢሠራ፣
4. በዚህ ሁኔታ ኀጢአት ቢሠራና በደለኛ ቢሆን፣ የሰረቀውን ወይም የቀማውን ወይም በዐደራ የተሰጠውን ወይም ጠፍቶ ያገኘውን ይመልሳል፤
5. በሐሰት የማለበትንም ሁሉ ይመልስ፤ የበደል መሥዋዕቱን በሚያቀርብበት ጊዜ የወሰደውን በሙሉ የዋናውን አንድ አምስተኛ በመጨመር ለባለ ንብረቱ ይመልስ።
6. ከመንጋውም እንከን የሌለበትን ዋጋው ተመጣጣኝ የሆነ አውራ በግ ስለ በደሉ መሥዋዕት አድርጎ ለእግዚአብሔር (ያህዌ) ለማቅረብ ወደ ካህኑ ያምጣ፤
7. በዚህም ሁኔታ ካህኑ በእግዚአብሔር (ያህዌ) ፊት ያስተሰርይለታል፤ ሰውየውም ስለ ፈጸመው ስለማንኛውም በደል ይቅር ይባላል።
8. እግዚአብሔር (ያህዌ) ሙሴን እንዲህ አለው፤
9. “አሮንና ልጆቹን እንዲህ ብለህ እዘዛቸው፤ ‘ስለሚቃጠለው መሥዋዕት አቀራረብ የምትከተለው ሥርዐት ይህ ነው የሚቃጠለው መሥዋዕት ሌሊቱን ሁሉ እስኪነጋ ድረስ በመሠዊያው ላይ ባለው ማንደጃ ላይ ይቀመጥ፤ እሳቱም በመሠዊያው ላይ ዘወትር ሲነድ ይደር።
10. ካህኑም ከበፍታ የተሠራ የውስጥ ሱሪውን ካጠለቀ በኋላ፣ የበፍታ ቀሚሱን ይልበስ፤ እሳቱ በመሠዊያው ላይ መሥዋዕቱን ከበላው በኋላ የሚቀረውን ዐመድ አንሥቶ፣ በመሠዊያው አጠገብ ያፍስስ።
11. ከዚያም ልብሱን አውልቆ ሌላ ልብስ ይቀይር፤ ዐመዱንም ተሸክሞ ከሰፈር ውጭ በአምልኮው ሥርዐት መሠረት ንጹሕ ወደ ሆነ ስፍራ ይውሰድ።