ዘሌዋውያን 4:23-35 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

23. ኀጢአት መሥራቱን በተረዳ ጊዜ እንከን የሌለበትን ተባዕት ፍየል የግሉ መሥዋዕት አድርጎ ያቅርብ።

24. እጁንም በፍየሉ ራስ ላይ ይጫን፤ የሚቃጠል መሥዋዕት በሚታረድበትም ስፍራ በእግዚአብሔር (ያህዌ) ፊት ይረደው፤ ይህም የኀጢአት መሥዋዕት ነው።

25. ካህኑም ከመሥዋዕቱ ደም በጣቱ ጥቂት ወስዶ የሚቃጠል መሥዋዕት የሚቀርብበትን መሠዊያ ቀንዶች ይቅባ፤ የተረፈውንም ደም ሁሉ በመሠዊያው ግርጌ ያፍሰው።

26. የኅብረት መሥዋዕቱን እንዳቃጠለ ሁሉ ሥቡንም በሙሉ በመሠዊያው ላይ ያቃጥል፤ በዚህም መሠረት ካህኑ የሰውየውን ኀጢአት ያስተሰረይለታል፤ ሰውየውም ይቅር ይባላል።

27. “ ‘ከሕዝቡ መካከል አንዱ ሰው ባለማወቅ ኀጢአት ቢሠራ፣ እግዚአብሔር (ያህዌ) አታድርጉ ብሎ ከከለከላቸው ትእዛዛት አንዱን ተላልፎ ቢገኝ እርሱ በደለኛ ነው።

28. ኀጢአት መሥራቱን በተረዳ ጊዜ፣ እንከን የሌለባትን እንስት ፍየል ስለ ፈጸመው ኀጢአት የግሉ መሥዋዕት አድርጎ ያቅርብ።

29. እጁን ለኀጢአት መሥዋዕት በቀረበችው ፍየል ራስ ላይ ይጫን፤ የሚቃጠል መሥዋዕት በሚታረድበት ስፍራም ይረዳት።

30. ካህኑ በጣቱ ከደሟ ጥቂት ወስዶ የሚቃጠል መሥዋዕት የሚቀርብበትን መሠዊያ ቀንዶች ይቅባ፤ የተረፈውንም ደም ሁሉ በመሠዊያው ግርጌ ያፍሰው።

31. ሥቡን ከኅብረት መሥዋዕት በወጣበት አኳኋን ሥቡን ሁሉ ያውጣ፤ ካህኑም ሽታው እግዚአብሔርን (ያህዌ) ደስ የሚያሰኝ መሥዋዕት አድርጎ በመሠዊያው ላይ ያቃጥለው፤ በዚህም መሠረት ካህኑ የሰውየውን ኀጢአት ያስተሰርይለታል፤ ሰውየውም ይቅር ይባላል።

32. “ ‘ስለ ኀጢአት መሥዋዕት የበግ ጠቦት የሚያቀርብ ከሆነ፣ እንከን የሌለባትን እንስት ያቅርብ።

33. እጁን በጠቦቷ ራስ ላይ ይጫን፤ የሚቃጠል መሥዋዕት በሚታረድበት ስፍራም የኀጢአት መሥዋዕት አድርጎ ይረዳት።

34. ካህኑም ከኀጢአት መሥዋዕቱ ደም በጣቱ ጥቂት ወስዶ የሚቃጠል መሥዋዕት የሚቀርብበትን መሠዊያ ቀንዶች ይቅባ፤ የተረፈውንም ደም ሁሉ በመሠዊያ ግርጌ ያፍሰው።

35. ሥቡ ከኅብረት መሥዋዕት ጠቦት በወጣበት አኳኋን ሥቡን ሁሉ ያውጣ፤ ካህኑም በመሠዊያው ላይ ለእግዚአብሔር (ያህዌ) በእሳት በሚቀርበው መሥዋዕት ላይ ያቃጥለው። በዚህ መሠረት ሰውየው የሠራውን ኀጢአት ካህኑ ያስተሰርይለታል፤ ሰውየውም ይቅር ይባላል።

ዘሌዋውያን 4